የሁለተኛ ዲቪዝዮን ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛውን ዙር ዛሬ ተጀምሯል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሁለተኛው ዙር ጨዋታ ዛሬ በሀዋሳ ተጀምሯል፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ቂርቆስ ሲረታ ባህር ዳር ከተማ እና ወጣቶች አካዳሚ አቻ ተለያይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ሁለተኛው ዙር ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በሀዋሳ የሰው ሰራሽ ሳር ሜዳ ላይ ተጀምረዋል፡፡ረፋድ 4፡00 ሲል ንፋስ ስልክ ላፍቶን ከ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አገናኝቶ ጥሩ ፉክክርን አሳይቶን በንፋስ ስልክ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ተስፋ ሰጪ የሆኑ አዳዲስ ፊቶች ባየንበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኖቹ ብዙውን ደቂቃ በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ ተገድበው የቆዩ ቢሆንም ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ ግን ለዕይታ ሳቢ ነበር፡፡ የጠሩ የግብ አጋጣሚዎች መመልከት ባንችልም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ 23ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምትን አግኝው ቅድስት ማቲዮስ መትታ የንፋስ ስልኳ ግብ ጠባቂ መሠረት ተፈራ በግሩም ሁኔታ አድናባታለች፡፡

ንፋስ ስልክ ላፍቶዎች በሁሉም ረገድ ተሽለው በታዩበት ሁለተኛ አጋማሽ በሶስት ደቂቃ ልዩነት ሁለት ጎሎችን አስቆጥረዋል፡፡ 50ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር ወደ መሀል በመሳብ ጥሩ እንቅሴቃሴን በማድረግ ለቡድኗ ልዩነት ስትፈጥር የነበረችው ጡባ ሀሰን በግሩም አጨራረስ ጎል አስቆጥራ ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ከግራ መስመር እየተነሳች ጥሩ እንቅስቃሴን ለቡድኗ ስታደርግ የነበረችው ሜሮን ግርማ ከመረብ አዋህዳ ጨዋታው በንፋስ ስልክ 2 ለ 0 የበላይነት ተጠናቋል፡፡

10፡00 ሲል ዲቪዚዮኑን እየመራ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚን አገናኝቷል፡፡ ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የአካዳሚ የበላይነት የታየበት የነበረ ቢሆንም ኳስን ከመረብ ለማገናኘት ግን የነበራቸው ጥረት እምብዛም የተሳካ አልነበረም፡፡በተለይ አርያት ኦዶንግ፣ ንግስት በቀለ እና የምስራች ሞገስ ወደ ፊት ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችሉም ከጎል ጋር ሊታረቁ ግን አልቻሉም፡፡ 

ባህር ዳሮች በአንፃሩ የመልሶ ማጥቃትን አጨዋወት ተከትለው ወደ ሜዳ ቢገቡም ጠንካራውን የአካዳሚ ተከላካይ ለማለፍ ግን አልቻሉም፡፡ ጨዋታው እንደ ማራኪነቱ ግቦችን ሳያስመለከትተን 0ለ0 ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ