የአርባምንጭ ከተማ የሴቶች ቡድን የመኪና አደጋ ገጠመው

በአዳማ ከተማ እየተደረገ ባለው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊ የሆነው የአርባምንጭ ከተማ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በዛሬው ዕለት የመጓጓዣ አውቶብሱ ላይ የመገልበጥ አደጋ ገጥሞታል፡፡

በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታውን ትናንት በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ክለቡ አድርጎ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5 ለ 0 የተሸነፈው ቡድኑ ዛሬ ማለዳ ላይ ቀለል ያለ የማለቀቂያ ልምምድ ለመሥራት በዛው አዳማ በተከራየው ቅጥቅጥ አይሱዙ ከያዘበት ሆቴል ወደ ስታዲየም እያመራ ባለበት ወቅት ከፊት ለፊቱ የሚመጣውን ባለሦስት እግር መኪና (ባጃጅ) ለማለፍ ባደረገው ቅፅበታዊ ውሳኔ መኪናው ተገልብጦ በውስጡ ያሉ የክለቡ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ላይ ጉዳት አስተናግዷል፡፡

በተለይ የክለቡ ሁለት ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ ጥላሁን ከበድ ያለ ጉዳት የጠማቸው ሲሆን ከአስራ አምስት የማያንሱ ተጫዋቾች ደግሞ በገጠማቸው ቀላል ጉዳት በአዳማ ኃይለማርያም ሪፈራል ሆስፒታል ዛሬ ቀኑን ሙሉ በህክምና ሲረዱ ቆይተዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት በአሁኑ ሰዓት ተጎጂዎቹ በቂ የህክምና ክትትል እያደረጉ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የታወቀ ሲሆን ከአደጋው የተረፉት አባላትም ፌዴሬሽኑ፣ ዶክተር እንደገና አለምአዋሶ፣ አሰልጣኝ መሠረት ማኔ፣ ጋዜጠኛ ዳግም ዝናቡ እና ጋዜጠኛ ዳዊት ሀብቴን ከዚህም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ላደረጉላቸው ርብርብ አመስግነዋል። የሌሎች ክለቦች አሰልጣኞች እና ተጫዋቾችም በሆስፒታል በመገኘት የተጎዱትን ሲጠይቁ ተስተውሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ