ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ በጎል ሲንበሸበሽ ሆሳዕና እና ሀላባም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የምድብ ለ ሦስተኛ ሳምንት ዛሬ ሲቀጥል ሀላባ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማ ድል ቀንቶቸዋል።

አስቀድሞ ከታወቁት ተሳታፊ ቡድኖች የአንድ ሳምንት ጨዋታ ከተደረገ በኃላ ወልቂጤ ከተማ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ ሲሆን በአንፃሩ አሰላ የመጀመርያውን ሳምንት አራፊ በመሆን ሁለተኛ ሳምንትን ጨዋታውን ካደረገ በኃላ ሀሰተኛ የኮቪድ ምርመራ ውጤት በማቅረቡ ከውድድሩ እንዲሰረዝ ሲደረግ ዋና አሰልጣኙ ለአንድ ዓመት ቡድን መሪው ለስድስት ወር ከማንኛውም እግርኳሳዊ እንቅስቃሴ መታገዳቸው ታውቋል።

በተዘበራረቀ ሁኔታ ሦስተኛ ሳምንት በደረሰው የምድብ ለ ጨዋታ ጠዋት ረፋድ ላይ ሀላባ ከተማ ከ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ በበርበሬዎቹ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በቀድሞ ተጫዋች አሰልጣኝ ዳንኤል ሀብታሙ እየተመሩ በአንፃራዊነት በዕድሜ የተሻለ ቡድን ይዘው በመቅረብ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም ያገኙት ግልፅ የጎል አጋጣሚ ተረጋግተው አለመጠቀማቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በተለይ ባመከናቸው ኳሶች ኮከብ ሆኖ የዋለው የሀላባ ግብጠባቂ ሰላሙ በቀለ ብቃት ቡድኑን ታድጓል።

የመጫወት ፍላጎታቸው ከፍ ያለው እና ከእረፍት መልስ ጎል ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት በርበሬዎች ሦስት ግልፅ የሆነ የጎል አጋጣሚ ፈጥረው በመጨረሻም በረከት ዓለሙ ከጎሉ ፊት ለፊት ከሰጥኑ ጫፍ መሬት ለመሬት በመምታት ባስቆጠራት ጎል አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። በረከት ዓለሙ በተከታታይ ጨዋታ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች መሆኑን እያሳየ ይገኛል።

ስምንት ሰዓት የተካሄደው ሁለተኛ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናን ከ አዲስ አበባ አገናኝቶ ደስታ ዋሚሾ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ሆሳዕና ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። አዲስ አበባ ከተማ ምንም እንኳን በተከታታይ ሦስት ጨዋታ ሽንፈት ቢያስተናገድም ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ መምጣቱ የዛሬው ጨዋታ አመላካች የነበረ ቢሆንም እንቅስቃሴያቸው በጎል ያልታጀበ በመሆኑ ጥረታቸው መና ሆኖ ለመሸነፍ ተገደዋል።

በጨዋታው ጎል ለማስቆጠር ተቸግረው የነበሩት ሆሳዕናዎች ከዕረፍት መልስ በሊጉ ከወዲሁ አምስት ጎል በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን እየመራ የሚገኘው ደስታ ዋሚሾ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደ ጎልነት ቀይሮት አሸናፊ ሆነዋል። ለጎሉ መቆጠር የቢንያም ሀይሉ ሚና የጎላ ነበር። ለጎል ያለው ዕይታ፣ የአጨራረስ ብቃቱ እና የቦታ አያያዙ አስደናቂ የሆነው ደስታ ተገቢውን ትኩረት እና ክትትል የሚያገኝ ከሆነ የወደፊቱ ምርጥ አጥቂ ሆኖ እንደሚወጣ ከወዲሁ መናገር ይቻላል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በአዳማ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ መካሄዱን ቀጥሎ አዳማ ከተማ ከግማሽ ደርዘን በላይ ጎል አስቆጥሮ አሸንፎ መውጣት ችሏል።

የከተማው አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ አለማድረጉን ተከትሎ ከውድድር ውጭ ሆኑ ሲባል ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አበባው ለውድድሩም ሆነ ለቡድኑ የሚያስፈልገውን ወጪ በሙሉ በመሸፈን የአንድ ሳምንት ጨዋታ ካመለጣቸው በኃላ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት ሠራተኞቹ ለውድድሩ በቂ ቅድመ ዝግጅት አለማድረጋቸውን ተከትሎ በአዳማ ከተማ በርከት ያሉ ጎሎችን ለማስተናገድ ተገደዋል።

በሱፍቃድ አበበ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን የጀመሩት አዳማዎች ቢኒያም አይተን አራት ጎሎች የጎል መጠናቸውን ወደ አምስት አድርሰዋል። ቢንያም አይተንም በውድድሩ ከሀድያው ደሰታ ዋሚሾ ቀጥሎ ሐት ትሪክ የሰራ ሁለተኛ ተጫዋች መሆን ችሏል።

በጨዋታው ብልጫ የነበራቸው አዳማዎች በላይ ጌታቸው ዮናስ አብነት እና በዮሐንስ ፈንታ ተጨማሪ ጎሎች አስቆጥረው የጎል መጠናቸውን ወደ ስምንት አድርሰዋል። ባሳለፍነው ጨዋታ ጎል ማስቆጠር የቻለው ምንተስኖት ዮሴፍ ብቸኛውን የወልቂጤን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአዳማ 8-1 አሸንፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ