አዳማ ከተማ ራሱን በፋይናንስ ለማጠናከር እንቅስቃሴ ጀመረ

ያጋጥመው የፋይናንስ ችግር ህልውናውን እየተፈታተነው የሚገኘው አዳማ ከተማ ራሱን በገቢ ለማጠናከር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ጀምሯል።

ወደ ሊጉ ከተመለሰበት 2007 ወዲህ በሊጉ ጠንካራ ቡድን በመገንባት የሚታወቀው አዳማ ከተማ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ የቀድሞው ጥንካሬው እየከዳው መሆኑ ተስተውሏል። በተለይም በገንዘብ እጥረት ወሳኝ ተጫዋቾቹን ለማቆየት ያልቻለ ሲሆን ዘንድሮም ደካማ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።

ክለቡን በበላይነት እየመሩ የሚገኙት አካላት ይሆን ጉዞ ለማስተካከል እንዲረዳ ያለበትን የገንዘብ ዕጥረት ለመቅረፍ እንቅስቃሴ እያደረጉ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ከአንበሳ ቢራ ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ለመፈፀም መነጋገራቸው ታውቋል። ክለቡ እና የአንበሳ ቢራ (ዩናይትድ ቤቨሬጅስ) ዓምና የስፖንሰርሺፕ ስምምንት ለመፈፀም ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም ኮሮና ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ ስምምነቱ ሳይደረግ መቅረቱ ይታወሳል። ከዛ ወዲህ የውድድር መቋረጥ እና የአመራር ለውጥ መደረግ ስምምነቱ በእንጥልጥል እንዲቀር አድርጎት ቆይቷል።

የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ገመቹ መኮንን የደጋፊዎች ፕሬዝዳንት አቶ ምስክር ሰለሞን እና አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል በተገኙበት የአንበሳ ቢራ የህግ አማካሪ እና የማርኬቲንግ ክፍል ኃለፊው ባሉበት ትናንት ከሰዓት በሪፍት ቫሊ ሆቴል ንግግር አድርገዋል። በአብዛኛው ሁኔታ ላይ ቅድመ ስምምነት እያደረጉ መሆኑን የሰማን ሲሆን በቅርቡም ይፋዊ ስምምነት ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

የክለቡ የሥራ አስፈፃሚ አባላት በአቶ ገመቹ መኮንን እየተመሩ ተጨማሪ የክለቡን አቅም የሚያጠናክሩ ድርጅቶችን በማናገር ስፖንሰር ለማግኘት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ