የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ እና ሐ አስረኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አስረኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ የተደረጉ ሲሆን በምድብ ለ ሀላባ ከተማ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ኢኮሥኮ፤ በምድብሐ ኮልፌ ቀራኒዮ ሙሉ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል፡፡

4፡00 ሲል ሀምበሪቾ ዱራሜን ከ ሀላባ ከተማ አገናኝቷል፡፡ ተጠባቂ በነበረው እና ብርቱ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የሀምበሪቾዎች ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት የነበረ ቢሆንም ሀላባዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ቅርፅ በመግባት ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ በአምስተኛው ደቂቃ ላይ የሀምበሪቾው የመስመር ተጫዋች አምረላ ደልታታ እጅጉን ለግብ የቀረ አጋጣሚን አግኝቶ መጠቀም ሳይችል የቀረበት ቀዳሚዋ የጨዋታው ሙከራ ነበረች፡፡ በእንቅሴቃሴ ሳቢ የነበረ ነገር ግን የጠሩ አጋጣሚዎችን ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር መመልከት ያልቻልን ሲሆን ሀላባ ከተማዎች ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ጥቂት ደቂቃ ሲቀር በእዩኤል ሳሙኤል አማካኝነት ያልተሳካ ሙከራን ማድረግ ችለዋል፡፡

ውጥረቶች ነግሰው በታዩበት በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኳስን በመቆጣጠር ሁለቱም ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድን መከተል ቢችሉም ሀላባ ከተማዎች የፈጠሩት ፈጣን የሽግግር እንቅስቃሴ ጎል እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ 65ኛው ደቂቃ ላይ ሰይድ ግርማ ከቀኝ የሀምበሪቾ የግብ ክልል ውስጥ እየገፋ ገብቶ የተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም ጎል አስቆጥሮ ሀላባን መሪ አድርጓል፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኃላ ኃይላቸውን ወደ ማጥቃት ሽግግሩ በይበልጥ በማድረግ ጥቃት ለመሰንዘር የሞከሩት ሀምበሪቾዎች በተደጋጋሚ ወደ ሀላባ ግብ ክልል ቀይረው ባስገቧቸው ተጫዋቾች አማካኝነት ሲደርሱ ተስተውሏል፡፡ 81ኛው ደቂቃ ላይ ከሀላባ የግብ ክልል ፊት ለፊት ዳግም በቀለ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ሲተፋው ከቀኝ በኩል ሾልኮ በመግባት ተቀይሮ የገባው ብሩክ ኤልያስ ኳስን እና መረብን ቢያገናኝም በረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሽራለች፡፡ በስታዲየሙ የታደሙትንም ሆነ የሀምበሪቾን የቡድን አባላት ያበሳጨችው ከጨዋታ ውጪ ውሳኔን በመቃወም በረዳት ዳኛው ላይ ክስ አስይዘዋል፡፡ ጨዋታው በዚህ ምክንያት አምስት ደቂቃ ዘግይቶ በድጋሚ ጀምሯል፡፡

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በአምረላ ደልታታ አማካኝነት ሀምበሪቾዎች አቻ ለመሆን መቃረብ ቢችሉም መሳካት ሳይችል ጨዋታው 1 ለ 0 በሀላባ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሀምበሪቾው አጥቂ ዳግም በቀለ ጨዋታው የሀላባን ተጫዋች ሆን ብለህ ተማተሀል በሚል ቀይ ካርድ ተመልክቷል፡፡ ሀምበሪቾዎችም ከዳኛው የሪፖርት ክስ በተጨማሪ ክሳቸውን በፅሁፍ አስገብተዋል፡፡

ከሰአት 8፡00 ሲል ጅማ አባቡና እና አዲስ አበባ ከተማን አገናኝቶ በአዲስ አበባ ከተማ 3 ለ 0 የበላይነት ተደምድሟል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክር ቢታይበትም የአዲስ አበባ ከተማ ከጎል ጋር ያላቸው ቁርኘት የተሻለውን ቦታ ይወስዳል፡፡18ኛው ደቂቃ የሺዋስ በለው ከቀኝ አቅጣጫ ሰብሮ በመግባት ጎል አስቆጥሮ መዲናይቱን ክለብ ቀዳሚ አድርጓል፡፡

አባቡናዎች ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ወደ ጎል የመቀየር ችግር ይታይባቸው እንጂ ወደ ጎል በመድረስ ግን አይታሙም። ሆኖም በተከላካይ ስፍራ ይስተዋልባቸው የነበሩ ክፍተቶች ተጨማሪ ጎል እዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል፡፡ ከእረፍት መልስ 69ኛው ደቂቃ ላይ የሺዋስ የሰጠውን ጥሩ ኳስ ዘርአይ ገብረሥላሴ ከመረብ አዋህዶ የአዲስ አበባን የግብ መጠን ከፍ አድርጓል፡፡ ሰይድ ሰጠኝ መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ አምስት ብቻ ሲቀረው ተጨማሪ ጎል አክሎ ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 3 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የምድቡ የመጨረሻ የዚህ ሳምንት ጨዋታ በአቃቂ ቃሊቲ እና ኢኮሥኮ መካከል የተደረገ ነበር። በአሰልጣኝ ዳዊት ታደለ እና ዳንኤል ገብረማርያም መካከል መከባበር በታየበት በዚህ ጨዋታ ተመሳሳይ የጨዋታ ቅርፅን በሁለቱም ክለቦች መካከል መመልከት ብንችልም የአቃቂ ተጫዋቾች ግላዊ ስህተት ለኢኮሥኮዎች መልካም አጋጣሚን የፈጠሩ ሆነዋል፡፡ 28ኛው እና 70ኛው ደቂቃ አጥቂው የኃላሸት ሰለሞን ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለክለቡ አስገኝቷል፡፡

ምድብ ሐ

በምድቡ የሳምንቱ ሁለተኛ ቀን ውሎ የጠዋት ጨዋታ የካ ክ/ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን አንድ አቻ ተለያይተዋል። ሚኪያስ አምሐ ባስቆጠረው ጎል የካዎች ለረጅም ደቂቃዎች መምራት ችለው የነበረ ቢሆንም በ87ኛው ደቂቃ ቤንጃሚን በራሱ ላይ ያስቆጠረው ጎል መድን ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል

ቀጥሎ የተደረገው የጌዴኦ ዲላ እና ከንባታ ሺንሺቾ ጨዋታ በተመሳሳይ አንድ አቻ ተጠናቋል። በሁለተኛው ደቂቃ አላዘር ዘውዱ ዲላን ቀዳሚ ሲያደርግ ኤፍሬም ታምራት በ70ኛው ደቂቃ ሺንሺቾን አቻ አድርጓል።

የዘንድሮው የምድቡ ክስተት ቡድን ኮልፌ ቀራኒዮ ከመሪው ያለውን ልዩነት አጥብቦ ደረጃውን ያሻሻለበትን የ1-0 ድል ቡታጅራ ከተማ ላይ አስመዝግቧል። በ88ኛው ደቂቃ አንዋር ዱላ ብቸኛዋን የኮልፌ የድል ጎል ማስቆጠር ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ