በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ11 ሳምንት የሦስተኛ ቀን ውሎ የመጨረሻ ጨዋታ በጌዲኦ ዲላ እና አቃቂ ቃሊቲ መካከል ተደርጎ በጌዲኦ ዲላ 3ለ1 የበላይነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው አስቀድሞ ትንግርት የሴቶች ስፖርት ለጌዲኦ ዲላው አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ በአንደኛው ዙር ይዞ ለቀረበው ምርጥ የቡድን ስብስብ ሽልማት አበርክቶለት ጨዋታው ተጀምሯል፡፡ ገና ከጅምሩ አቃቂ ቃሊቲዎች በገነት ፈርዳ የ1ኛ ደቂቃ የቅጣት ምት ሙከራ አጀማመራቸው አስፈሪ የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ እየወረዱ መጥተው ለጌዲኦ ዲላ እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡ በ1ኛው ደቂቃ ላይ አቃቂዎች ካደረጉት የቅጣት ምት ሙከራ ሁለት ደቂቃ ብቻ እንደተቆጠረ በቅፅበታዊ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በረጅሙ ከመሀል ሜዳ በተላከ ኳስ አጥቂዋ ቱሪስት ለማ ወደ ግብ ክልል ገፍታ በመግባት የአቃቂዋ ግብ ጠባቂ ስርጉት ተስፋዬ ስትመልሰው ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረችው ይታገሱ ተገኝወርቅ ወደ ጎልነት ለውጣው ዲላን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡
በይበልጥ ወደ አቃቂ የግብ ክልል ሲደርሱ የታዩት ጌዲኦ ዲላዎች በመልሶ ማጥቃት ፈጣን ሽግግር በአቃቂ ላይ ብልጫን ወስደው ለመጫወት ችለዋል፡፡ 20ኛው ደቂቃ ላይ በርካታ ተጫዋቾቹን በኮቪድ 19 በማጣቱ አማራጭ ተጫዋቾቹን መጠቀም ያልቻለው እና በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሶስቱኅ ብቻ ለማስቀመጥ የተገደደው አቃቂ ቃሊቲ በድጋሚ ጎል ተቆጥሮበታል፡፡ ሰላማዊት ጎሳዬ ከቀን በኩል በመግባት የሰጠቻትን ኳስ ተጠቅማ እፀገነት ግርማ ወደ ጎሎነት ለውጣው ጌዲኦ ዲላን ወደ 2 ለ 0 አሸጋግራለች፡፡
ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ አሁንም ጌዲኦ ዲላ በተሻለ መነቃቃት ብልጫን ያሳዩ የነበረ ሲሆን ደቂቃዎች እስኪገፉ ድረስ ግን አቃቂዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት አድርጓል፡፡ የአሰልጣኝ ብዙአየው ዋዳው ቡድን ኳስን ለመያዝ ከሞከሩ በኃላ ወደ ፊት መስመሩ በሚያሻግሩበት ወቅት ሁነኛ አጥቂ ባለመኖሩ የተገኙ ዕድሎችን በማምከን በተቃራኒው ለጌዲኦ ዲላ ምቹ የማጥቃት ሀይል በር የከፈተን ደካማ የመከላከል መንገድን አስተውለናል፡፡ በዚህም የግራ እግር ተጫዋቿ እፀገነት ግርማ ከግራ በኩል ስታሻማ ቱሪስት ለማ ወደ ጎልነት ለውጣው የዲላዎችን የግብ መጠን ወደ ሶስት አሳድገዋል፡፡
በመልሶ ማጥቃት ሦስት ጎሎች ከተቆጠረባቸው በኃላ ለመጫወት የሞከሩት አቃቂዎች በኬፊያ አብዱራህማን አማካኝነት ወደ ጨዋታ የመለሳቸውን ጎል አስቆጥረው 3 ለ 1 ወደ መሆን ተሸጋግረዋል፡፡ ጌዲኦ ዲላዎች በተደጋጋሚ በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ሊያስቆጥሩባቸው የሚችሉ በርካታ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም መረጋጋት የተሳነው የአጥቂ ክፍሉ የተገኙትን መልካም ዕድሎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡በጭማሪ ደቂቃ አቃቂዎች በአስናቀች ትቤሶ አማካኝነት ብረት ገጭታ በተመለሰችሁ ኳስ ሙከራን ያደረጉ ቢሆንም ጨዋታው በጌዲኦ ዲላ 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
-በጨዋታው የሀዋሳ ከተማው የህክምና ባለሙያ ዘሪሁን ዳዊት የአቃቂ የህክምና ባለሙያ በኮቪድ 19 በመያዟ በግል ፍላጎቱ ለአቃቂዎች የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የታየ ሲሆን ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ ደግሞ የአዳማ ስታዲየም የመጫወቻ ሳሩ ውሀ ሲጠጣበት የነበረበት መንገድ ሊበረታታ የሚገባው እና ለሜዳዎቻችን አመቺነትም አስተዋጽኦ ላቅ ያለ በመሆኑ ይቀጥል የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እንወዳለን፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ