የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ እና ሐ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ከስድስቱ ጨዋታዎች አንድ ብቻ በመሸናነፍ ተጠናቋል።
ምድብ ለ
ረፋድ 04:00 ላይ የተደረገው የሻሸመኔ ከተማ እና ጅማ አባ ቡና ጨዋታ ያለ ጎል ሲጠናቀቅ ከሰዓት 08:00 ላይ ኢኮሥኮ እና ቤንችማጂ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። ቤዛ መድኅን በ18ኛው ደቂቃ ኢኮሥኮን ቀዳሚ ሲያደርግ ጆቴ ገመቹ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመርያ ቤንችማጂን አቻ አደርጓል። የዕለቱ የምድቡ የማሳረጊያ ጨዋታ የነበረው የነቀምቴ ከተማ እና ሀላባ ከተማ ጨዋታም ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ምድብ ሐ
ጠዋት 2:00 ላይ ቡታጅራ ከተማን ከ ጌድኦ ዲላ ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ዘላለም አበራ ዲላን በ68ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ማድረግ ቢችልም ክንዴ አቡቹ በ82ኛው ደቂቃ ቡታጅራን አቻ ማድረግ ችሏል።
ረፋድ ላይ በወራጅ ቀጠናው የሚገኙት ሺንሺቾ እና ቂርቆስን ያገናኘው ጨዋታ ሺንሺቾ 2-0 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችሏል። ለሺንሺቾ አዱኛ ገብረመድን በ47ኛው እንዲሁም ምንተስኖት ታምሬ በ85ኛው ደቂቃ ግቦችን ያስቆጠሩ ተጨዋቾች ናቸው።
ከሰዓት በኋላ የምድቡ መሪ አርባምንጭን ከ አርሲ ነገሌ ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ያለምንም ግብ በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በሁለቱም ቡድን በኩል መረጋጋት ያልነበነበት እና አሰልቺ ገፅታ የነበረው ጨዋታው በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የጎል አጋጣሚ ተፈጥሮበት ነበር። ሙና በቀለ አክርሮ የመታው ኳስ ተጨርፎ በነፃ አቋቋም ላይ ወደነበረው የቡድን አጋሩ በላይ ገዛኸኝ ቢያመራም በላይ አክርሮ መቶት ተደርቦ የወጣበት እንዲሁም በ5ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው አሸናፊ ታደሰ ከቀኝ መስመር ይዞ ገብቶ በሞከረው ኳስ አርባምንጮች ለጎል ቀርበው ነበር።
በቀሪው ክፍለ ጊዜ የኃይል አጨዋወት የተስተዋለበት ጨዋታው ሌላ ሙከራ ለመመልከት ረጅም ደቂቃ አስጠብቋል። በ30ኛው ደቂቃ በላይ ገዛኸኝ የሞከረውን ኳስ የአርሲ ነገሌ ግብጠባቂ ያከሸፈበት እንዲሁም አርሲዎች በ35ኛ ደቂቃ ቱፋ ተሺታ አማካኝነት ካደረጎት ብቸኛ ሙከራ ውጭ ሌላ ሙከራ ሳንመለከት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ አዞዎቹ ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት ተጭነው መጫወት ሲችሉ አርሲ ነገሌዎች በአንፃሩ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ለመሄድ በማሰብ በጥንቃቄ ሲከላከሉ ተስተውሏል።
በአርባምንጭ በኩል በቡታቆ ሸመድ፣ ፍቃዱ መኮንን እና አብነት ተሾመ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም የአርሲ ነገሌ ግብጠባቂ ሚኪያስ ሂጃ የሚቀመስ አልሆነም። ጨዋታውም ምንም ግብ ሳያስመልክት መጠነቃቁን ተከትሎ መሪው አርባምንጭ በ23 ነጥብ እንዲሁም ነገሌ አርሲ 14 ነጥቦችን በመሰብሰብ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ