ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 11ኛ ሳምንት ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ እና አዲስ አበባ መካከል ተደርጎ 1 ለ 1 ተጠናቋል፡፡

በሁለቱም በኩል ይህ ነው የሚባል የጎላ እንቅስቃሴ መመልከት ባንችልም በመጀመሪያው አጋማሽ አዲስ አበባ ከተማዎች ከቆሙ ኳሶች ያደርጓቸው በነበሩ ሙከራዎች ከሀዋሳ ተሽለው ታይተዋል፡፡ በተለይ አማካይዋ ትርሲት መገርሳ በሁለት አቅጣጫዎች የተገኙትን የቅጣት ምቶች በቀጥታ መትታ ዓባይነሽ ኤርቄሎ በግሩም ሁኔታ ያወጣችባት አጋጣሚዎች ለአዲስ አበባዎች አስቆጪ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ረጃጅም ኳስ ላይ ትኩረት ያደረጉት ሀዋሳዎች በበኩላቸው የአጥቂዎቻቸው ደካማ የአጨራረስ ብቃት ያገኟቸውን ያለቀላቸው ዕድሎች እንዳይጠቀሙ ዳርጓቸዋል፡፡ 33ኛው ደቂቃ ላይ አይናለም አሳምነው ከቀኝ አቅጣጫ ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ሰጥታት አጥቂዋ መሳይ ተመስገን ሁለቴ ብቻ ገፋ በማድረግ ወደ ጎል ብትመታውም ግብ ጠባቂዋ ተስፋነሽ ተገኔ በሚገርም ብቃት ያዳነችባት ሀዋሳ ከተማን ምናልባት መሪ የምታደርግ ብትሆንም ወደ ጎልነት መለወጥ ሳትችል ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ የተለየ የጨዋታ ቅርፅን እንመለከታለን የሚል ተስፋ የነበረ ቢሆንም ረጃጅም እና የሚባክኑ ኳሶች የበዙበትን አጋማሽ የተመለከትን ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች ግብ ጠባቂያቸው ዓባይነሽ ኤርቄሎን በጉዳት ካጡ በኃላ በይበልጥ መቀዝቀዞች ታይቶባቸዋል፡፡ሆኖም ረጃጅም ኳሶቻቸው አስፈሪ በመሆናቸው ከአዲስ አበባ በተሻለ ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን አግኝተዋል፡፡ 58ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል እየገፋች ገብታ አክርራ ስትመታው የአዲስ አበባዋ ግብ ጠባቂ ተስፋነሽ ተገኔ በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሏ ከግቡ ትይዩ የነበረችው ነፀነት መና በቀላሉ ወደ ጎልነት ለውጣው ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በይበልጥ መነቃቃት ይታይባቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም መዳከም የተንፀባረቀባቸው ሀዋሳዎች ከቆመ ኳስ ግብ አስተናግደዋል፡፡ 63ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሀዋሳ የግብ አቅጣጫ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት ላይ አዲስ አበባ ከተማዎች ያገኙትን ቅጣት ምት ትርሲት መገርሳ አክርራ መታ ከተደጋጋሚ ሙከራዎች በኃላ ጎል አስቆጥራ ክለቧን አቻ አድርጋለች፡፡ ለዚህች ጎል መቆጠር ተቀይራ የገባችው ግብ ጠባቂዋ ገነት ኤርሚያስ ስህተት ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ከመስመር የተሻማ ኳስ የአዲስ አበባዋ አጥቂ ድንቅነሽ በቀለ አግኝታው ወደ ጎል ስትመታ ከግቡ ጠርዝ ላይ ካሰች ፍሰሀ አውጥታው ሀዋሳን ታድጋ በመጨረሻም ጨዋታው 1 ለ 1 ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ