የከፍተኛ ሊጉ ሁለተኛ ዙር የሚደረግባቸው ስፍራዎች እና የዝውውር ቀናት ይፋ ተደርጓል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድቦች የመጀመርያ ዙር እስከ ቀጣይ ሳምንት ሲጠናቀቅ የሁለተኛ ዙር የሚጀምርበት ጊዜ እና የሚካሄድበት ስፍራ ታውቋል።

በ2013 ውድድር ዓመት ባቱ (ዝዋይ) በሚገኘው የሼር ኢትዮጵያ ስታዲየም፣ በሀዋሳ አርቲፊሻል ሳር ሜዳ እንዲሁም በድሬዳዋ ስታዲየም እየተከናወነ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል። የምድብ ሀ አስቀድሞ ሲጠናቀቅ የምድብ ለ ሁለት ሳምንታት፣ የምድብ ሐ ደግሞ አንድ ሳምንት መርሐ ግብር ካከናከኑ በኋላ የመጀመርያው ዙር ውድድር ሙሉ ለሙሉ የካቲት 15 ይጠናቃል ተብሎ ይጠበቃል።

አወዳዳሪው አካል ትናንት ለቡድኖች በላከው ደብዳቤ የምድብ ሀ በሀዋሳ፣ የምድብ ለ በወልዲያ እንዲሁም የምድብ ሐ በነቀምቴ ከተሞች ውድድራቸውን እንዲያከናውኑ ተገልጿል።

የሦስቱም ምድቦች የተጫዋቾች ዝውውር የሚደርጉበት ቀን ይፋ የሆነ ሲሆን ከየካቲት 23 እስከ መጋቢት 13 ድረስ ዝውውሩን እንዲከናውኑ ተወስኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ