​ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

በነገ ከሰዓቱ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ሰበታ ከተማ በሽንፈት እና በአቻ ውጤቶች ከሰነበተባቸው ሰባት ሳምንታት በኋላ አዳማ ላይ ድል ቀንቶት ነበር ወደ ዕረፍት ያመራው። ከአደጋ ዞኑ ብዙ ያልራቀ ደረጃውን ለማሻሻል ግን የነገዎቹ ሦስት ነጥቦች ያስፈልጉታል።

ሰበታ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ሜዳ ላይ ያሳየው መነቃቃት ደካማ ጎኖቹ ቀንሰው በመታየታቸው ጭምር የሚገለፅ ነበር። ተደጋጋሚ ስህተቶች የማያጡት የቡድኑ የተከላካይ ክፍል የተሻለ መረጋጋት አሳይቶ በሁለት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ ወጥቷል። የጎንዮሽ ቅብብሎቹ በርክተው ወደ ፊት መጠጋትን መድፈር ሲሳነው የነበረው ቡድን በተሻለ ሁኔታ ለተጋጣሚ የግብ ክልል ቀርቦ ሲንቀሳቀስም አስተውለናል። ነገር ግን አሁንም በተጋጣሚ የግብ ክልል ዙሪያ የሚታይበት አለመረጋጋት በሊጉ ዝቅተኛ ግብ በማስተናገድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ካለው ወልቂጤ ጋር ሲገናኝ የግብ ዕድሎችን በብዛት እንዳይፈጥር ሊያረገው ይችላል። በዚህ ረገድ የወልቂጤ የኋላ ክፍል ላይ ከአንድ በላይ አስገዳጅ ለውጦች ሊኖሩ መቻላቸው ለሰበታ መልካም ዜና ነው

በሌላ በኩሉ ቡድኑ እንደ ያሬድ ሀሰን ፣ መስዑድ መሀመድ ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ፉዓድ ፈረጃ ዓይነት ተጨዋቾቹን ከጉዳት እና ቅጣት መልስ ማግኘቱ ለአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን ለአማራጮች መብዛት ፈተና ሊዳርግባቸው እንደሚችል ይታሰባል። አሰልጣኙ ነገ ከረጅም ጊዜ በኋላ አዳማ ላይ ድል ያስገኘላቸውን ስብስብ ከተመለሱ ተጫዋቾቻቸው ጋር የሚያቀናጁበት መንገድ እና በጨዋታው ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል።

ሰበታ ከታማ ከላይ ከተጠቀሱት ወደ አገልግሎት ከሚመለሱለት ተጨዋቾች ውጪ ዳንኤል ኃይሉን በቅጣት የሚያጣ ሲሆን በስብስቡ ውስጥ ጉዳት ያለበት ሌላ ተጨዋች ግን የለም።

እስካሁን ሁለት ጊዜ ብቻ ሽንፈት ያገኘው ወልቂጤ ከተማ ወጣ ገባ በሚል አቋም ከሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ብሎ የሚገኝ ሲሆን ወደ ላይኛው ፉክክር ለመጠጋት ሰበታን ማሸነፍ ይኖርበታል።

ወልቂጤ ከተማ ከሰፊው ስብስቡ ላይ ስዩም ተስፋዬ ፣ አሚን ነስሩ እና አብዱርሀማን ሙባራክ ጋር ተለያይቶ የባህር ዳሩን ውድድር ይጀምራል። የተጋጣሚዎችን የማጥቃት አማራጮች በመዝጋት ጨዋታው ከባድ እንዲሆንባቸው በማድረግ የማይታማው የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቡድን ከነገ ተጋጣሚው አንፃር አማካይ ክፍል ላይ በቁጥር በርከት ብሎ የኳስ ስርጭቶች ወደ ሜዳው እንዳይገቡ በማድረግ በመልሱ በሁለቱ መስመሮች በኩል ጥቃት ለመሰንዘር የሚችልበት ዕድል ይኖራል።

ከዚህ ሂደት ተጠቃሚ ለመሆን ግን በድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ ብልጭ ብሎ ሀዋሳ ላይ መደገም ያልቻለውን የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ስልነት ያስፈልገዋል። ቡድኑ አዘውትሮ የሚያሳየው የሜዳ ላይ ትጋት ግን ሰበታ ከተማም ተመሳሳይ ስሜት ላይ ሊገኝ ከመቻሉ ጋር ሲታሰብ በጨዋታው አማካይ ክፍል ላይ የሚኖረውን ፍልሚያ ይበልጥ ወሳኝ ሊያደርገው ይችላል። ነገ ለወልቂጤ ስጋት የሚሆነው የግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ የስዩም ተስፋዬ መውጣት እና የተስፋዬ ነጋሽ መጎዳት ሲሆን ይህም ቡልቻ ሹራን ለማቆም ፈተና ሊሆንበት ይችላል።

ወልቂጤዎች ዳግም ንጉሴ ፣ ተስፋዬ ነጋሽ እና በኃይሉ ተሻገርን በጉዳት ምክንያት የማይጠቀሙ ሲሆን ፍሬው ሰለሞን እና አልሳሪ አልመሀዲ ልምምድ ጀምረዋል። 

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በተሰረዘው የውድድር ዓመት ሰበታ ከተማ 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት ዓሎ

ጌቱ ኃይለማርያም – መሳይ ጻውሎስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

መስዑድ መሀመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ – አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ
                              

ፍፁም ገብረማርያም  – እስራኤል እሸቱ – ቡልቻ ሹራ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

አዳነ በላይነህ – ቶማስ ስምረቱ – ተስፋዬ መላኩ – ረመዳን የሱፍ

ያሬድ ታደሰ– ሀብታሙ ሸዋለም– አብዱልከሪም ወርቁ 

አቡበከር ሳኒ – ሄኖክ አየለ – አሜ መሐመድ