የአሠልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-0 ባህር ዳር ከተማ

ያለግብ ከተጠናቀቀው የ12ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው?

ተጋጣሚያችን ወደ ኋላ ተጠግቶ እንደሚጫወት ከመጀመሪያውም አውቀን ነበር። በትዕግስት ኳሶችን ተቀባብለን እድሎችን ለመፍጠር ነበር የሞከርነው። ግን የመጨረሻው የሜዳ ክልል ላይ ውሳኔዎቻችን በአብዛኛው ስህተት ነበሩ። ብዙ የጎል ዕድሎችን መፍጠር አልቻልንም። እነሱ ኋላ ላይ በጣም ተጠቅጥቀው ስለሚከላከሉ ያንን መስበር ተቸግረን ነበር።

ቡድኑ የሚያገኛቸውን የፍፁም ቅጣት ምቶች ስላለመጠቀሙ?

ዛሬ የመጀመሪያ የፍፁም ቅጣት ምት መቺያችን ባዬ ነው። ጥሩ ግብ አግቢያችንም ነው። የፍፁም ቅጣት ምት በዕለቱ በመቺው የሚወሰን ነው። ዛሬ ነጥብ ላለማግኘታችን እሱን ብቻ ተጠያቂ አላደርግም። እርግጥ በመጨረሻ ሰዓት ጨዋታውን የምናሸንፍበት ዕድል ነበር። ግን እንደ ቡድንም በምንፈልገው መልኩ የጎል ዕድሎችን አልፈጠርንም።

ቡድኑ ስላለበት ደረጃ?

እኔ ቡድኔ እንዲሆንልኝ በምፈልገው ደረጃ ላይ አልተገኘም። ይህንን ግን በሁለተኛው ዙር ለማስተካከል እንሞክራለን።

ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው?

በመከላከሉ ረገድ የነበረን እንቅስቃሴ መልካም ነው። በተለይ ከተጋጣሚያችን የማጥቃት ጥንካሬ አንፃር ተከላክለን የምናገኛቸውን ኳሶች በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ነበር ያሰብነው። ነገር ግን የመጨረሻው የማጥቂያ ሲሶ ላይ የነበረው ሀይላችን ትንሽ ደከም ያለ ነበር። እንደታየው ተጋጣሚያችን ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ ነበር። ነገር ግን እኛ የመጠቀም ችግር ነበረብን። እንዳልኩት ግን በመከላከሉ ረገድ የነበረን ነገር ጥሩ ነበር። እርግጥ መጨረሻ ላይ የነበረው ነገር እንደ ስህተት እንወስደዋለን። የግብ ጠባቂውም ብቃት አንድ ነጥብ ይዘን እንድንወጣ የድርሻውን ተወቷል።

ስለ ቡድኑ የጨዋታ መንገድ እና ቀጣይ ጨዋታዎች?

ሁል ጊዜ በመልሶ ማጥቃት የምትጫወት ከሆነ ከፊት ያለው ተጫዋች በጣም ስለሚሮጥ ይደክምብሃል። በዚህ ላይ ደግሞ ጨዋታው የሚደረገው ቀጥር ላይ ስለሆነ ፀሀይ እና የአየር ሁኔታው ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። ይህንን ተከትሎ ማስተካከል ያለብንን ነገር በቀጣይ እናስተካክላለን።

አንደኛውን ዙር ማጠናቀቅ ስለሚፈልጉበት ደረጃ?

የእኛ የመጀመሪያው እቅድ ከዚህ ከአደገኛው ቀጠና በአሳማኝ ሁኔታ ወጥቶ የሊጉ አጋማሽ ላይ ካሉ ቡድኖች ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የሚል ነው። ከዚህ መነሻነት ቀጣዩንም ጨዋታ በዚህ ልክ በማየት ነው ወደ ሜዳ የምንገባው።


© ሶከር ኢትዮጵያ