የ12ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ መርሐ-ግብር የሆነው የሰበታ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ በሰበታ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።
አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ አዳማ ከተማን ካሸነፉበት ቋሚ 11 አራት ለውጦች አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ጌቱ ኃይለማርያም፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ዱሬሳ ሹቢሳን በአለምአየሁ ሙለታ፣ መስዑድ መሀመድ፣ ዒብራሂም ከድር እና ፍዓድ ፈረጃ ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል። በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመሩት ወልቂጤዎች በበኩላቸው ከሀዋሳ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ ዳግም ንጉሴን እና ተስፋዬ ነጋሽን በይበልጣል ሽባባው እና ፍሬው ሰለሞን ቀይረው ጨዋታውን ጀምረዋል።
እንደ ጠዋቱ የሊጉ መርሐ ግብር ሁሉ ይህኛውም ጨዋታ የካቲት 12 ታስቦ የሚውለውን የሰማዕታት ቀን ለአንድ ደቂቃ በቆየ የህሊና ፀሎት በማሰብ ተጀምሯል።
ገና ጨዋታው በተጀመረ በ25ኛው ሰከንድ በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ሰበታዎች የግብ ክልል የደረሱት ወልቂጤዎች በአሜ መሐመድ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው በትሪቡን የሚገኙት የዕለቱ ረዳት ዳኛ ከጨዋታ ውጪ በሚል ግቡ ተሽሮባቸዋል። የጨዋታውን የመጀመሪያ ፈጣን ሙከራ ያደረጉት ወልቂጤዎች ወደ ግብነት የቀየሩት ዕድል ቢሻርባቸውም በድጋሜ የተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መጎብኘት ቀጥለዋል። በዚህም በአሜ እና አብዱልከሪም አማካኝነት ቀዳሚ ለመሆን ታትረዋል። በተቃራኒው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ከኳስ ውጪ ጊዜን ሲያሳልፉ የነበሩት ሰበታዎች የመሐል አጥቂያቸው ፍፁም ገብረማርያምን ዒላማ ያደረጉ የመስመር ላይ ተሻጋሪ ኳሶችን ሲሞክሩ ተስተውሏል።
የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው የታዩት ወልቂጤዎች በ24ኛው ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ሰበታዎች የግብ ክልል ደርሰው አሜ መሐመድ ከአብዱልከሪም ወርቁ በተሻገረለት ነገርግን አሜ በአስቆጪ ሁኔታ ባመከነው ዕድል ለግብ ቀርበው ነበር። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከ13 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ መሐል ለመሐል ጥቃት ለመሰንዘር የጣሩት ሰበታዎች በፍፁም የርቀት ኳስ መሪ ለመሆን ከጫፍ ደርሰው ነበር። በአስገዳጅ ጉዳት አንድ አንድ ተጫዋቾቻቸውን ገና አጋማሹ ሳይገባደድ የቀየሩት ሁለቱ ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በአንፃራዊነት በሁለተኛው አጋማሽ ተነቃቅተው ወደ ሜዳ የገቡ የሚመስሉት ሰበታዎች የጨዋታው የበላይ ለመሆን ጥቃቶችን በተደጋጋሚ በግራ መስመር በኩል በማተኮር ለመሰንዘር ጥረዋል። በተቃራኒው በዚህኛው አጋማሽ አጨዋወታቸውን ገድበው ሲጫወቱ የነበሩት ወልቂጤዎች በ62ኛው ደቂቃ በሄኖክ አማካኝነት ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥረዋል። ከደቂቃዎች በኋላ ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስለው ሰበታዎች ተቀይሮ በገባው ዱሬሳ አማካኝነት ለግብነት የቀረበ ዕድል ፈጥረዋል። በጨዋታው ጅማሮ ያስቆጠሩት ጎል ከጨዋታ ውጪ በሚል የተሻረባቸው ወልቂጤዎች በድጋሚ በአሜ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው በአወዛጋቢ ሁኔታ ከጨዋታ ውጪ ተብለዋል።
ጨዋታው ቀጥሎም በ69ኛው ደቂቃ የመዓዘን ምት ያገኙት ሰበታዎች አጋጣሚውን በታደለ አማካኝነት አሻምተውት የተገኘውን ኳስ መሳይ በግንባሩ ወደ ግብ መትቶት የግቡ ቋሚ ሲመልሰው በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ፍፁም ገብረማርያም ኳስ እና መረብን አገናኝቶ መሪ ሆነዋል። በ72ኛው ደቂቃ በድጋሜ የቅጣት ምት ያታገኙት ሰበታዎች አጋጣሚውን በታደለ አማካኝነት ወደ ግብ መትተው መሪነታቸውን ለማሳደግ ቢጥሩም የወልቂጤው የግብ ዘብ ጀማል ኳሱን አምክኖታል።
ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ እጅግ እየተጋጋለ የመጣው ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ክፍት እንቅስቃሴን ማስመልከት ጀምሯል። መሪ የሆኑት ሰበታዎች በቡልቻ፣ ታደለ እና ፍፁም አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያለሙት ወልቂጤዎች ደግሞ በሄኖክ እና አህመድ አማካኝነት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በተለይም ተቀይሮ የገባው አህመድ ሁሴን በ84ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብነት የቀረበ ዕድል አግኝቶ አምክኗል።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በርከት ያሉ ሙከራዎችን ያስመለከተው መርሐ-ግብሩ ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በሰበታ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሰበታ ከተማዎች ያገኟቸውን ነጥቦች 13 በማድረስ 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ወልቂጤዎች ደግሞ በሰበሰቧቸው 16 ነጥቦች ባሉበት 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ