​ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ተከታታይ ደረጃ ላይ ያሉትን ቡድኖችን የሚያገናኘውን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና ነገም አሸናፊነቱን በማስቀጠል ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ለማድረግ ወደ ሜዳ ይገባል።

በመጨረሻው የሲዳማ ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ የሚፈልጉትን ክፍተት ሁሉ መፍጠር የቻሉት ቡናዎች የማጥቃት ጉልበታቸው በዛ ልክ ሆኖ እንዲገኝ ጥረት ማድረጋቸው የሚቀር አይመስልም። ለዚህም ቡድኑ ለሚከተለው አጨዋወት ምቹ የሆነው ሜዳ እንደሚያግዘው ሲታሰብ የተጋጣሚው አጨዋወት ደግሞ ፈተና እንደሚሆንበት ይገመታል። በኳስ ቁጥጥር ብልጫቸው መነሻነት የግብ ዕድሎችን መፍጠሪያ ቀዳዳን ለማግኘት ብዙ ትዕግስት ያላቸው የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ልጆች በሊጉ ዝቅተኛውን የግብ መጠን ካስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ሲገናኙ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ክፍተት ባገኙበት ቅፅበት ሳያባክኑ በመጠቀም ብቃታቸው ጣራ ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል። ከተጋጣሚው ኃይል ተጠቃሚነት እና ታታሪነት አንፃርም የኢትዮጵያ ቡና ቅብብሎች ከወትሮውም ፈጠን ያሉ እና የአንድ ለአንድ ግንኙነትን የማይፈቅዱ ዓይነት መሆናቸውም አይቀርም። ቡድኑ በራሱ ሜዳ ላይም በሆሳዕና አጥቂዎች ጫና ሊደረግበት እንደሚችል ሲታሰብ በሲዳማው ጨዋታ ላይ ያልታየት ስህተቶቹ ካገረሹ ግን ላይቀጣ የሚችልበት ዕድል አይኖርም።

ሀዲያ ሆሳዕና ለሦስት ጨዋታዎች ርቆት የሰነበተውን ድል በቅርብ ተፎካካሪው ላይ ማሳካት ከቻለ የጅማ መጥፎ ትዝታውን ትቶ ወደ አዲስ አበባው ተፎካካሪነቱ ለመመለስ ጉዞ ይጀምራል።

ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ማስቆጠር የቻለው ሀዲያ ሆሳዕና ይህ ደካማ ጎኑን አስተካክሎ መቅረብ ተጋጣሚውን ከመቆጣጠር በላይ ሊከብደው ይችላል። በዚህ ረገድ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ባልተጠበቀ መልኩ ፊት ላይ ለውጦች አድርገው የገቡት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ነገ ግቦችን ለማግኘት ወደ ዳዋ ፣ ቢስማርክ እና ፎፋና ጥምረት ሊመለሱ ይችላሉ። ከመሰል ለውጦች እና በቅርብ ጨዋታዎች ላይ ካሳዩት ለማጥቃት ፍላጎት ከሚያሳይ የአደራደር እና የተጨዋቾች ምርጫ ሊመልሳቸው የሚችለው ግን የተጋጣሚያቸው ሙሉ ለሙሉ ማጥቃት ላይ ያተኮረ አቀራረብ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ቡና የሜዳውን ስፋት አብዝቶ የመጠቀም አዝማሚያ ያለው በመሆኑ ሆሳዕና በሦስት ተከላካዮች በሚጀምር አደራደሩ ጨዋታውን ለመጀመር የቴዎድሮስ በቀለን ቦታ በቀጥተኛ ለውጥ በመተካት በመስመር ተመላላሾቹ የግራ እና ቀኙን ኮሪደር ለመዝጋት እንዲያስብ ሊያደርገው ይችላል። ያም ካልሆነ እና ወደ አራት ተከላካዮች ፊቱን ካዞረ በሁለት አጥቂዎች ጥምረት ፊት ላይ ጫና በመፍጠር ከኳስ ጋርም ሲሆን እነርሱን በመልሶ ማጥቃት ለማግኘት በመሞከር ዕቅድ ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል።

ኢትዮጵያ ቡና ያለጉዳት እና ቅጣት መሉ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ የሰማን ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና የመሀል ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለን በጉዳት ከማጣቱ በተጨማሪ የዳዋ ሆቴሳ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ሁለቱንም ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ 2-1 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – ረመዳን ናስር – ዊሊያም ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – ሀብታሙ ታደሰ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-4-2)

መሀመድ ሙንታሪ

ሱለይማን ሀሚድ – ኢሴንዴ አይዛክ – ተስፋዬ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

 ቢስማርክ አፒያ – ተስፋዬ አለባቸው – አማኑኤል ጎበና – መድሀኔ ብርሀኔ

ሳሊፉ ፎፋና – ሚካኤል ጆርጅ