የአርባምንጭ ከተማ የሴት እግር ኳስ ቡድን በዛሬው ዕለት ልምምድ ጀምረዋል

በቅርቡ በአዳማ ከተማ ወደ ልምምድ ሲያመሩ በመኪና የመገልበጥ አደጋ ያስተናገዱት የአርባምንጭ ከተማ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ወደ መደበኛ ልምምዳቸው በዛሬው ዕለት ተመልሰዋል፡፡

ባሳለፍነው ሰኞ በአስረኛ ሳምንት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በንግድ ባንክ 5ለ0 ከተሸነፈበት ጨዋታ ማግስት ዕለተ ሰኞ ማለዳ ላይ ቀለል ያለ ልምምድ ለመስራት ወደ ስታዲየም ሲያመሩ ይዟቸው ይጓዝ የነበረው ሰርቪስ ተገልብጦ በተጫዋቾቹ ላይ ከባድ እና ቀላል ጉዳት አስተናግዶ እንደነበር እና ወደ ሆስፒታል አምርተው በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በኃላ አደጋው ከገጠማቸው ከአንድ ቀን ቆይታ በኃላ ወደ ነበሩበት ሆቴል እንደተጓዙ ይታወሳል፡፡

የክለቡ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች በአሁኑ ሰዓት በመልካም ጤንነት ላይ በመገኘታቸው በዛሬው ዕለት መደበኛ ልምምዳቸውን ጀምረዋል፡፡ ከቡድኑ አጠቃላይ ሀያ አምስት ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ ተጫዋቾች እንዲሁም ምክትል አሰልጣኙ ከበድ ያለ ጉዳት የደረሰባቸው በመሆኑ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን የቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ዛሬ ጠዋት በሆቴላቸው አቅራቢያ ቀለል ያሉ ልምምዶች መስራት ጀምረዋል። ከሰዓት ከነበረው የአቃቂ ቃሊቲ እና ጌዲኦ ዲላ ጨዋታ ቀጥሎም የቀኑ ሁለተኛ ልምምዳቸውን ሲሰሩ ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው መመልከት ችላለች፡፡

በአዳማ የሚገኙ ክለቦች እና ግለሰቦች ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ለተጫዋቾቹ ያደረጉት መልካም ተግባር የሚያስመሰግን ሲሆን እንደ ክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየው ንጉሴ ገለፃ የአምስት ወራት ደመወዝ ያልተከፈላቸውን ተጫዋቾች ወደ መደገፉም ሆነ ካለፉት በተሻለ ትኩረት ያልሰጧቸውን የሴት ቡድኑን በፋይናንስ ለማገዝ እየሰሩ እንደሆነ በአዳማ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል፡፡

ትናንት (ሀሙስ) በ11ኛ ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክተትሪክ ጋር ጨዋታ የነበረው ክለቡ ጨዋታው በተስተካካይ መርሀ ግብር በቀጣይ የሚደረግ ሲሆን በ12ኛው ሳምንት ግን ሀዋሳ ከተማን የፊታችን ሰኞ በመግጠም ወደ ውድድር ይመለሳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ