ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ፡ የምድቡ መሪዎች ሽንፈት ሲደርስባቸው ፋሲል እና ኮምቦልቻ ድል አስመዝግበዋል 

 

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 8ኛ ሳምንት 7 ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ተካሂደዋል፡፡ መሪዎቹ ነጠብ ሲጥሉ ተከታዮቻቸው ድል አድርገው ደረጃቸውን አሻሽለዋል፡፡

መቐለ ላይ የምድቡ መሪ የነበረው መቐለ ከተማ የመጨረሻ ደረጃን ይዞ በገጠመው አክሱም ከተማ ያልተጠበቀ 3-2 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ መቐለ 1-0 ከመመራት ተነስቶ 2-1 መምራት ቢችልም የኋላ ኋላ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡ ለአክሱም ጌታቸው ዘውዴ ሁለት ክብሮም አፅብሃ አንድ ሲያስቆጥሩ የመቐለን ቴዎድሮስ በሱፍቃድ እና ሀብታሙ ንጉሴ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

2ኛ ደረጃ ላይ የነበረው ወልድያ ወደ ባህርዳር ተጉዞ በባህርዳር ከተማ የ2-0 ሽንፈት ደርሶበታል፡፡ የባህርዳርን የድል ግቦች ተዘራ ጌታቸው እና ቴዎድሮስ ታደሰ አስቆጥረዋል፡፡
ተዘራ በ4 ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን የግቡንም መጠን 6 አድርሷል፡፡

ፋሲል ከተማ 3ኛ ደረጃ ላይ የነበረው አአ ከተማን አስተናግዶ 2-1 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡ የፋሲልን ሁለቱንም የድል ግቦች ከመረብ ያሳረፈው ሙሉቀን ታሪኩ ሲሆን የአአ ፖሊስን ብቸኛ ግብ የፋሲል ከተማው ተከላካይ ፍፁም በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯል፡፡

ወሎ ኮምቦልቻ ወልዋሎን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡ የወሎ ኮምቦልቻን የድል ግብ ሳምሶን ሚካኤል ከመረብ አሳርፏል፡፡

አበበ ቢቂላ ላይ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት በኢትዮጵያ መድን 2-0 ተሸንፏል፡፡ የሰማያዊዎቹን ሁቱንም የድል ግቦች ሀብታሙ ወልዴ አስቆጥሯል፡፡

የሜዳውን ጨዋታዎች አዲስ አበባ ላይ እንዲጫወት ጥያቄ አቅርቦ የተፈቀደለት ሙገር ሲሚንቶ መድን ሜዳ ላይ ቡራዩ ከተማን አስተናግዶ ካለግብ አቻ ሲለያይ ሱሉልታ ላይ ሱሉልታ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ በተመሳሳይ ካለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡

በዚሁ ምድብ ዛሬ ሊካሄድ የነበረው የሰሜንሸዋ ባህርዳር እና አማራ ውሃ ስራ ጨዋታ የደብረብርሃን ሜዳ ለኮንሰርት በመያዙ ምክንያት ጨዋታው ነገ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ በዚህም መሰረት ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን ነገ በ09፡00 ያደርጋሉ፡፡

የደረጃ ሰንጠረዡ ይህንን ይመስላል፡-

Untitled

ፎቶ – ውሃ ስፖርትን ያሸነፈው መድን

ያጋሩ