ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ አሰልጣኟን አገደ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊ የሆነው አዲስ አበባ ከተማ ዋና አሰልጣኙ ሙሉጎጃም እንዳለን ለስድስት ወራት አገደ ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ቦርድ ከሰሞኑ ባደረጉት ከፍተኛ ግምገማ ከ2012 ጀምሮ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ስትመራ የቆየችው ሙሉጎጃም እንዳለን ለስድስት ወራት ከክለቡ አሰልጣኝነት አግዷል፡፡ በስምንት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አአ ከተማ ከውጤት መጥፋት በተጨማሪ ስፖርተኞችን መከፋፈል፣ በአግባቡ አለመምራት፣ ከስፖርተኞች ጋር አብሮ ማደር እንዲሁም ጥቅምን ከተጫዋቾቹ መቀበል፣ የቡድኑ ረዳት አሰልጣኝ እና ቡድን መሪ ላይ ዛቻን ማሳደርን የመሳሰሉ ችግሮችን በአሰልጣኟ ላይ በመመልከቱ እግድ ማስተላለፉን ክለቡ ገልጿል፡፡

በአዳማ እየተደረገ በሚገኘው የሁለተኛው ዙር የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው አዲስ አበባ እስከ ውድድሩ ማብቂያ ድረስ በረዳት አሰልጣኟ የሺሀረግ ለገሰ እንዲሁም ሦስተኛ አሰልጣኝ በነበረው አሳምነው ገብረወልድ ጊዜያዊ አሰልጣኝነት እንደሚመራ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ለድረገፃችን ተናግረዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ