04፡00 ላይ የተካሄደው የኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማን ሲረታ ከተጠቀመበት አሰላለፍ ውስጥ ሚኪያስ መኮንን በሀብታሙ ታደሰ ቦታ ሲተካ ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ከጊዮርጊሱ ጨዋታ ሄኖክ አርፌጮ እና ዱላ ሙላቱን በቴዎድሮስ በቀለ እና መድሀኔ ብርሀኔ ምትክ ለውጧል።
የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች የተሻሉ ክፍተቶች የታዩባቸው እና ቡድኖቹ ወደ ግብ የቀረቡባቸውም ነበሩ። እንደተለመደው የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን የያዙት ቡናዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ ከአስራት ቱንጆ በተናሳ ኳስ ሰንጥቀው መግባት ሲችሉ አቡበከር ናስር አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። 6ኛው ደቂቃ ላይም አቤል ከበደ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገው ሙከራ ወደ ላይ ተነስቶበታል። ከዚህ በኋላ ግን ቡናዎች በሚፈልጉት መልኩ የሀዲያን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ሰብረው መግባት አልቻሉም። አብዛኛው እንቅስቃሴያቸውም በሜዳው አጋማሽ ላይ የቆየ ነበር።
ሲጀምሩ ለተጋጣሚያቸው ክፍተቶችን ትተው የታዩት ሀዲያዎች በቶሎ ወደ ጨዋታው መንፈስ ተመልሰው ከኳስ ውጪ የቡናን አማካዮች በአግባቡ በመቆጣጠር ኳስ ወደ ግብ ክልላቸው በአደገኛ ሁኔታ እንዳይደርስ አድርገዋል። በቀኝ መስመር ባመዘነ መልሶ ማጥቃትም አልፎ አልፎ ጫና ሲፈጥሩ 13ኛው ደቂቃ ላይ የቀኝ መስመር አማካዩ ዱላ ሙላቱ ከተነጠቀ ኳስ መነሻነት በፈጠረው ዕድል ሱለይማን ሀሚድ ያደረገው ጠንካራ ሙከራ በአቤል ማሞ ተመልሶበታል። ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ የአቤል ስህተትን ተከትሎ ካሉሻ አልሀሰን ጥሩ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ነበር። ያም ቢሆን ሆሳዕናዎች በቀሩት የአጋማሹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም።
ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያው በተጠናቀቀበት መንገድ የቀጠለ ነበር። ለጥንቃቄ የሰጡትን ትኩረት ይበልጥ ጨምረው የገቡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በራሳቸው የሜዳ ክልል ላይ ቀርተው ተጋጣሚያቸው የሚሰራውን ስህተት መጠበቅ መርጠዋል። ብሩክ ቃልቦሬን ጭምር ቀይረው በማስገባት የቡና አማካይ ክፍል ይበልጥ ክፍተት እንዳያገኝ ያደረጉትም ጥረት ሰምሮላቸዋል። ሙከራ ለማድረግ 74ኛው ደቂቃ ድረስ የጠበቁት ቡናዎችም ዊሊያም ሰለሞን ከሳጥን ውስጥ ባደረገው ሙከራ ለግብ ቢቀርቡም መሀመድ መንታሪ አምክኖባቸዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አቡበከር ናስር ሚኪያስ መኮንም በግንባሩ ባመቻቸለት ኳስ ከሙንታሪ ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም ሙከራው ወደ ውጪ ወጥቷል።
የሀዲያ ሆሳዕና የሁለተኛ አጋማሽ ሙከራዎች አብዛኞቹ የቡናው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ከግብ ክልሉ ወጥቶ ኳስ ለማደን ሲጥር ከሚፈጠሩ ስህተቶች የመነጩ ነበሩ። በአጋጣሚዎቹ የሀዲያ ተጫዋቾች ከርቀት ወደ ግብ የላኳቸው ኳሶች ግን ወደ ውጪ የሚወጡ ሆነዋል። ከሁሉም በላይ ቡድኑ 86ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ በእጅጉ ቀርቦ ካሉሻ አልሀሰን አቤል ማሞን አልፎ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ወደ ጎል የላከውን ኳስ ቢስማርክ አፒያ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ አመዝነው በዘለቁበት ሁኔታ የተገባደደው ጨዋታም ያለግብ ፍፃሜውን አግኝቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ