ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

የ12ኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።

በጅማው ስኬታማ ቆይታ በሰንጠረዡ አናት ላይ እንደተቀመጠ ወደ ባህር ዳር የመጣው ፋሲል ከነማ በውጤታማነቱ ለመቀጠል ነገ ጠጠር ያለ ተጋጣሚ ይጠብቀዋል። በአንፃሩ ከሰንጠረዡ ወገብ ከፍ የማለት ዕድላቸውን ከሦስት ተከታታይ ድል በኋላ ሌላ ሦስት ድል አልባ የጨዋታ ጉዞን አርገው ያመከኑት ሀዋሳዎች የሊጉን መሪ አስፈሪ ጉዞ የመግታት ፈተናን ይቀበላሉ።

ግብ ካስተናገዱ አምስት ጨዋታዎችን ያስቆጠሩት ፋሲል ከነማዎች እንደቡድን ከመከላከል ጥንካሬያቸው በዘለለ በተጨዋቾች ምርጫም ሆነ በአደረጃጀት የኋላ ክፍላቸው መረጋጋት ይታይበታል። ነገም የሀዋሳን የመስመር ጥቃት በአግባቡ ለማቆም ይህ የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በሁለቱ ኮሪደሮች ተጨማሪ ሽፋን እንደሚያገኝ ይጠበቃል። ከአጥቂ ጀርባ የሚሰለፉት አማካዮቹ የዘወትር ታታሪነትም ይህን ሚና ለመወጣት ብቁ የሚያረጋቸው ይመስላል። ከመከላከሉ ይልቅ ግን የቡድኑ የወገብ በላይ ክፍል በጨዋታው የጠሩ የግብ ዕድሎችን በብዛት ለመፍጠር እንዳይቸገር ያሰጋዋል።

ከድሬዳዋ ጋር እንደተመለከትነው ቡድኑ በቶሎ ግብ ለማግኘት ካለ ፈላጎት መነሻነት ቅርፅ ያለው የማጥቃት ሂደትን መተግበር ሲከብደው መታየቱ በተለይ ቀድሞ ግብ ካስተናገደ ወደ ጨዋታው ለመመለስ እንዳይቸግረው ያሰጋል። ከስብስብ አንፃር ግን ባለፈው ግብ ካስቆጠረው በዛብህ መለዮ በተጨማሪ የሱራፌል ጌታቸው ከቅጣት መመለስ ለአሰልጣኝ ስዩም ከበደ አማራጫቸውን የሚያሰፋላቸው ነው የሚሆነው። ቡድኑ በተመሳሳይ ከኳስ ውጪ ታታሪነት ከሚታይበት ቡድን ጋር እንደመግጠሙም የፊት መስመር ተሰላፊው መጂብ ቃሲም በግል ጥረቱ የሚፈጥራቸውን ዕድሎች አጥብቆ የሚፈልግበት አጋጣሚም ሊኖር ይችላል።

የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረቱ ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረ መሆኑ ከነገው ጨዋታ በፊት የሚያሳስበው ትልቁ ጉዳይ ነው። በመስመር ተከላካዮቹ ከፍ ያለ የማጥቃት ተሳትፎ ጭምር በፈጣን ጥቃት የግብ ዕድሎችን እየፈጠረ ተጋጥሚዎቹን የሚያስጨንቅበት ሂደት ተገማች የሆነ ይመስላል። በተከታታይ እንደተመለከትነውም ይህን ጠንካራ ጎኑን በመተንበይ ክፍተታቸውን ደፍነው ለሚመጡ ቡድኖችም በቂ ምላሽ ይዞ መምጣት አልቻለም። በእርግጥ ይህ ዋነኛው የማጥቃት አማራጩ በጉዳቶችን ጭምር ሳስቶ መታየቱ እና አሁን ላይ ተጫዋቼቹን መልሶ ማግኘቱ ወደ ጥንካሬው ይመልሰው እንደሆን ነገ የምንመለከተው ይሆናል።

ከፋሲል የማጥቃት ጉልበት አንፃርም ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ መረቡን ያላስደፈረው የሀዋሳ የኋላ ክፍል በመሀል በአዳማው ጨዋታ የታየበት ለመልሶ ማጥቃት በቀላሉ እጅ የመስጠት ምልክት ተመልሶ ከታየ ጨዋታው በእጅግ ሊከብደው ይችላል። ከሁሉም በላይ ግን በመልካም አቋም ላይ ሲገኙ ለቡድኑ የተመጣጠነ የመከላከል እና የማጥቃት እንቅስቃሴ ዋነኛ ተጠቃሽ የሆኑት እንደኤፍሬም ዘካርያስ እና ወንድምአገኝ ኃይሉ ዓይነት አማካዮች በተመሳሳይ ጥሩ አቋም ላይ ከሚገኙት የፋሲል አማካዮች ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ የጨዋታውን ውጤት የመወሰን ዕድሉ የሰፋ ነው።

በነገው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ከሰዒድ ሁሴን እና ቴዎድሮስ ጌትነት ውጪ ሌላ በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን ሀዋሳ ከተማም ጉዳት ላይ የነበሩ ተጫዋቾቹ ሁሉ ተመልሰውለታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ከ2009 በኋላ ቡድኖቹ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ሀዋሳ 2 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ፋሲል 1 አሸንፏል። በሦስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ሀዋሳ 10 ፤ ፋሲል 8 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሐንስ

ኤፍሬም ዘካርያስ – ዳዊት ታደሰ – ወንድምአገኝ ኃይሉ

ኤፍሬም አሻሞ – መስፍን ታፈሰ – ብሩክ በየነ

ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)

ሚኬል ሳማኬ

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንዳሻው – ሀብታሙ ተከስተ

በረከት ደስታ – ሱራፌል ጌታቸው – ሽመክት ጉግሳ

ሙጂብ ቃሲም


© ሶከር ኢትዮጵያ