ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ፡ አአ ከተማ ነጥብ ሲጥል ወራቤ ከተማ እና ናሽናል ሴሚንት ጣፋጭ ድል አስመዝግበዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 8ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ መሪው አዲስ አበባ ከተማ ባልተጠበቀ ሁኔታ ነጥብ ጥሏል፡፡ ናሽናል ሴሚንት የሳምንቱን ከፍተኛ ድል ሲያስመዘግብ ወራቤ ከተማ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ድል ይዞ ተመልሷል፡፡

08፡00 አበበ ቢቂላ ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያደረጉት ጨዋታ ካለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ አአ ከተማ የምድቡ መሪ እንደመሆኑ አአ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንደመገኘቱ የጨዋታው ውጤት ያልተጠበቀ ነበር፡፡

ድሬዳዋ ላይ ናሽናል ሴሚንት ፌዴራል ፖሊስን አስተናግዶ 4-0 አሸንፏል፡፡ መሃመድ ጀማል 3 ግቦች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሲሰራ ሰይፈ ገብርኤል አንዷን ግብ አስቆጥሯል፡፡ የሐት-ትሪክ ጀግናው መሃመድ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራቸውን ግቦች 6 ማድረስ ችሏል፡፡

ወደ ጅማ ያቀናው ወራቤ ከተማ ጅማ ከተማን 3-1 አሸንፏል፡፡ የወራቤን የድል ግቦች መሃመድ ከድር ፣ የሺጥላ ዳዲ እና ፈቱረሂም ሴቾ ሲያስቆጥሩ የባለሜዳውን ቡድን ግብ ሳሙኤል አሸብር ከመረብ አሳርፏል፡፡

ሀዋሳ ላይ 8 ግቦች በተስተናገዱበት ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ ከ አርሲ ነገሌ 4-4 ተለያይተዋል፡፡ ለደቡብ ፖሊስ ወንድሜነህ አይናለም 2 ሲያስቆጥር ምስጋናው ወልደዮሃንስ እና ሚካኤል ለማ ቀሪዎቹን አስቆጥረዋል፡፡ ለአርሲ ነገሌ አገኘሁ ልኬሳ ፣ ኄኖክ ሙሉጌታ ፣ ሙሉቀን አዲሱ እና የደቡብ ፖሊሱ ሙሉነህ ገብረመድህን በራሱ መተረብ ላይ አስቆጥረዋል፡፡ የደቡብ ፖሊሱ አማካይ ወንድሜነህ አይናለም በ4 ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሲያስቆጥር የግቡን መጠንም 8 በማድረስ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ከወልድያው እዮብ ወልደማርያም ጋር መምራት ጀምሯል፡፡

ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ከ ድሬዳዋ ፖሊስ ፣ ጅንካ ላይ ጅንካ ከተማ ከ ሀላባ ከተማ ካለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡

በዚህ ምድብ ዛሬ ሊደረግ የነበረው የባቱ ከተማ እና የጅማ አባ ቡና ጨዋታ የባቱ 8 ተጫዋቾች በመታመማቸው ለነገ 09፡00 የተዛወረ ሲሆን ጅማ አባ ቡና የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ የምድቡን መሪነት ከአዲስ አበባ ከተማ ይረከባል፡፡

ነቀምት ከ ነገሌ ቦረና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በነገሌ ቦረና ስራ አስፈጻሚ እና የከተማው ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ህልፈት ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡

የደረጃ ሰንጠረዡ ይህንን ይመስላል፡-

Untitled

 

ፎቶ – በ4 ተከታታይ ጨዋታዎች 6 ግብ ያስቆጠረው ወንድሜነህ አይናለም

ያጋሩ