ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል አግኝቷል

የ12ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን መርሐ-ግብሮች መካከል አንዱ የሆነው የጅማ አባጅፋር እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በጅማ አባጅፋር 1-0 አሸናፊነት ተገባዷል።

በዛሬው ዕለት አዲሱ ቡድናቸውን መምራት የጀመሩት የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች ከ11ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር መጠነኛ ለውጦችን አድርገው ለጨዋታው ቀርበዋል። ጅማዎች ቡድናቸው ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ሀብታሙ ንጉሴን በሙሉቀን ታሪኩ እንዲሁም ሮባ ወርቁን በአብርሃም ታምራት በመለወጥ ጨዋታውን ጀምረዋል። በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመሩት ሲዳማዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና 5-0 ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ ሰንደይ ሙትኩ፣ ግርማ በቀለ እና አዲሱ አቱላን በፈቱዲን ጀማል፣ ግሩም አሠፋ እና ተመስገን በጅሮንድ ቀይረዋል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው በማድረግ ጨዋታውን የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በ6ኛው ደቂቃ የተገኘን የመዓዘን ምት በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ነገርግን አጋጣሚውን ወደ ግብነት ለመቀየር የጣረው የቡድኑ አምበል ፈቱዲን ጀማል የሞከረውን የግንባር ኳስ ተከላካዮች መልሰውታል። ቡድኑ ይህንን ለግብነት የቀረበ ሙከራ ከሰነዘረም በኋላ በደቂቃዎች ልዩነት ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ወደ ጅማ የግብ ክልል ለማድረስ ሞክሯል። በተቃራኒው ረጃጅም ኳሶችን ለቡድኑ አጥቂዎች በማድረስ ጨዋታውን የቀጠሉት ጅማዎች በጥሩ መግባባት የሲዳማዎችን ጥቃት መመከት ይዘዋል። በመስመር ላይ በሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጥቃት መሰንዘር የቀጠሉት ሲዳማዎች በ22ኛው ደቂቃ ማማዱ ሲዲቤ ለሀብታሙ ገዛኸኝ አቀብሎት ሀብታሙ ባልተጠቀመበት ዕድል ሌላ አጋጣሚ ፈጥረዋል።

ከኳስ ጀርባ በመሆን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን መጠቀም የፈለጉ የሚመስሉት ጅማዎች በ23ኛው ደቂቃ ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል ተጉዘው ሊሞክሩት በነበረ ኳስ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃም የሲዳማው የመሐል ተከላካይ ፈቱዲን ጀማል ተመስገን ደረሰ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ በዕለቱ ዋና ዳኛ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሱራፌል አወል አስቆጥሯል። በድጋሜ በ30ኛው ደቂቃ ሌላ የቆመ ኳስ ያገኙት ጅማዎች መሪነታቸውን ለማስፋት ቢጥሩም ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ሙከራቸውን አክሽፎባቸዋል። የፊት መስመራቸው ፍጥነት እና መዋለል በመጠቀም ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩት ሲዳማዎች በአብዛኛው በቀኝ መስመር ተከላካዩ አማኑኤል አንዳለ የሚነሱ ኳሶችን ለመጠቀም ቢጥሩም ግብ ሳያስቆጥሩ አጋማሹ ተጠናቋል።

የአጥቂ መስመራቸው ላይ ለውጥ በማድረግ ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ሲዳማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ሲታይባቸው የነበረውን የስልነት ችግር ለማስተካከል ቢያልሙም ሀሳባቸው ሳይሰምር ቀርቷል። በተቃራኒው ውጤት ለማስጠበቅ አጋማሹን የጀመሩት ጅማዎች ኳስን ለመቆጣጠር ብዙም ፍላጎት ሳያሳዩ ትኩረታቸውን መከላከል ላይ በማድረግ ጨዋታውን ቀጥለዋል።

የጅማን ጠንካራ የተከላካይ ክፍል በቀላሉ ማስከፈት ያልቻሉት ሲዳማዎች በዚህኛው አጋማሽ ማማዱ ሲዲቤን ዒላማ ያደረጉ የመስመር ላይ ተሻጋሪ ኳሶችን እና ከሳጥን ውጪ የሚመቱ ጥብቅ ኳሶችን ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክረዋል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም በ77ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል የግብ ክልሉ ሳጥን ላይ የደረሰው ቡድኑ በዳዊት አማካኝነት ሙከራ አድርጎ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው በረከት አውጥቶበታል። በተጨማሪም በ86ኛው ደቂቃ የጅማ ተከላካይ ለግብ ጠባቂው ኳስ ሲያቀብል በፍጥነት የደረሰው ጫላ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ተቃረቦ ነበር። ነገርግን የጅማዎችን የተከላካይ መስመር መስበር ሳይችሉ ጨዋታው ተገባዷል።

ውጤቱን ተከተሎም የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ያገኙት ጅማዎች ነጥባቸውን 7 በማድረስ አንድ ደረጃን አሻሽለው 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ሲዳማዎች በ11 ነጥብ ያሉበት 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ