የከፍተኛ ሊጉ ክለብ የመኪና አደጋ ገጠመው

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ክለብ የመኪና አደጋ ማስተናገዱ ተሰምቷል።

በድሬዳዋ ሲደረግ በነበረው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ ውድድር ተሳታፊ በመሆን የአንደኛውን ዙር ያጠናቀቀው የነገሌ አርሲ ክለብ በዛሬው ዕለት ቡድኑን ይዞ ሲጓዝ የነበረው መኪና አደጋን ማስተናገዱ ታውቋል፡፡ ቡድኑ ውድድሩን አጠናቆ በዛሬው ዕለት ከድሬዳዋ ወደ ነገሌ አርሲ ከተማ ሲያመራ አዳማ መግቢያ ላይ ተጫዋቾቹን እና የቡድኑን አባላት የያዘው መኪና አደጋ አስተናግዷል፡፡ መንገድ ስቶ የመጣን ተሳቢ መኪና አድናለው በማለት ተጫዋቾቹን የያዘው ሹፌር የመሪውን አቅጣጫ ሲቀይር አደጋው ሊከሰት እንደቻለም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ በአደጋው አንድ የቡድኑ ተጫዋች መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዱ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ያመራ ሲሆን ሌሎች የቡድኑ የአሠልጣኝ አባላት እና ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በተመሳሳይ በቅርቡ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተካፋይ የሆነው የአርባምንጭ ከተማ የሴቶች ክለብ የመኪና አደጋን ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ