በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ጎሎች በማስቆጠር በአዲሱ ክለቡ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው በረከት ደስታ ስለወቅታዊ አቋሙ ይናገራል።
ሻሸመኔ ተወልዶ ያደገው ወጣቱ የመስመር አጥቂ በአምቦ ፕሮጀክት በመግባት እግርኳስን በአካዳሚ ሰልጥኖ ወጥቷል። የአዳማ እግርኳስ ክለብ የዚህን ወጣት አቅም ተረድቶ በ2008 አጋማሽ ላይ ተስፋ ቡድኑን ተቀላቅሎ በከስድስት ወራት በኃላ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ችሏል። አራት ዓመት ባሳለፈው የአዳማ ቆይታው እድገቱን ጠብቆ ድንቅ የሚባሉ ጊዜዎችን አሳልፏል። ፈጣኑ የመስመር አጥቂ በእግርኳስ ህይወቱ ሁለተኛ ወደ ሆነ ክለቡ ዐፄዎቹ ቤት ዘንድሮ በመቀላቀል እየተጫወተ ይገኛል። በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ጎሎችን በማስቆጠር የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑኑ እያሳየ ይገኛል። ይህን ተከትሎ በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ በረከትን አግኝተን አውርተነዋል።
” የመጀመርያዎቹ አምስት ሳምንታት የነበረው እንቅስቃሴዬ ጥሩ ነበር። ያም ቢሆን ብዙ አጥጋቢ አልነበረም። ከዛ በኃላ ጅማ ላይ በነበረው ቆይታ አስቀድሞ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጬ ጨዋታዎችን በማየት ለምን እቀመጣለው በማለት እልህ ውስጥ ገብቼ አሁን ጥሩ ነገር እየሰራሁ እገኛለሁ።
” አሁን ከቡድኑ ጋር እየተላመድኩ ነው። አዲስ ቡድን እንደመሆኑ እስክላመድ በእንቅስቃሴ ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር ለመቀናጀት ተቸግሬ ነበር። እንደኔ አጨዋወት አላገኘኋቸውም። አሁን ወደ እነርሱ አጨዋወት መጥቼ እየተላመድኩ ነው። በተከታታይ ሦስት ጨዋታ ከእነርሱ እየተግባባው ለመምጣቴ ማሳያ የሚሆነው ጎሎቼ እና አጨዋወቴ ምስክር ናቸው።
” እንደሚታወቀው ፋሲልን ዘንድሮ የተቀላቀልኩት ሁለተኛ ክለቤ ነው። ይህን ደግሞ በታሪክ የመጀመርያዬን የሊጉ ዋንጫ ከፋሲል ጋር ማንሳትን በጣም አስባለሁ። ለዚህም በጣም እርግጠኛ ነን ከፈጣሪ ጋር በቡድን መንፈሳችን እና የማሸነፍ ወኔያችን ዋንጫ እንደሚያነሳ የሚያስታወቅ በመሆኑ ዋንጫ እንደምናነሳ እገምታለው።
” ባለቤቴ ነፍሰ ጡር ናት፤ አሁን ዘጠኝ ወር ሆኗታል። በቅርቡ የልጅ አባት እሆናለሁ። እርሷን ለማሰብ ነው ጎሉን አግብቼ በዚህ መልኩ ኳሱን በሆዴ የያዝኩት። ባለፈው ጨዋታ ጎል ሳገባ ይህን ማድረግ ፈልጌ ረስቼው ነበር። አሁን ግን ፈጣሪ ሳትወልድ ሁለተኛ ዕድል ሰጥቶኝ ይህን በማድረጌ ደስ ብሎኛል።
“በመጨረሻ የቡድን አጋሮቼን በጣም አመሰግናለሁ። እነርሱ ባያግዙኝ ጎል አላገባም አናሸንፍም። ስለዚህ እነርሱን ማመስገን እፈልጋለው። በመቀጠል ፈጣሪዬን አመሰግናለው። ባለቤቴም በሰላም እንድትገላገል መልካም ምኞቴ ነው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ