የሳምንቱ ተጫዋቾችን የተመለከቱ ዐበይት ጉዳዮችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።
👉በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ የመጀመሪያ ግባቸውን ያስቆጠሩት ተጫዋቾች
ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን 4-2 በረታበት ጨዋታ አቤል እንዳለ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል በብርቱካናማ እና ቀዩ መለያ የመጀመሪያ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባለው አለመረጋጋት መቐለ 70 እንደርታ በሊጉ መካፈል አለመቻሉን ተከትሎ በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀናት ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው አማኑኤል ገ/ሚካኤል አዲሱን ቡድኑን ለመላመድ እና የቀደመውን ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን በፈረሰኞቹ ቤት ለማሳየት በተወሰኑ መልኩ ተቸግሮ ቆይቷል።
ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ግን ተጫዋቹ ወደ ቋሚ ተሰላፊነት መምጣቱን ተከትሎ የተሻለ እንቅስቃሴን ማድረግ እየቻለ ይገኛል። በዚህ የጨዋታ ሳምንትም አማኑኤል ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ከግብ ጋር ታርቋል።
በተመሳሳይ በደደቢት ቤት አስደናቂ ብቃቱን ማሳየቱን ተከትሎ በ2011 የክረምቱ የዝውውር መስኮት ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ወጣቱ አማካይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ግን ዕድገቱን ለማስቀጠል ተቸግሮ ከጥቂት ጨዋታዎች ውጭ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ለመቀጥ ተገዶ ተስተውሏል።
ነገር ግን ከረጅም ጊዜ በኃላ ቡድኑ አዳማን ሲረታ ያገኘው የቋሚነት ዕድል በመጠቀም ጥሩ እንቅስቃሴ ከማድረጉ ባለፈ በጨዋታው ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
👉ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሱት ይበልጣል ሽባባው እና አለልኝ አዘነ
አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛውን ተከትሎ ከኢኮሥኮ ወልቂጤ ከተማን የተቀላቀለው ይበልጣል ሽባባው በተሰረዘው የውድድር ዘመን የቡድኑ ተቀዳሚ የቀኝ መስመር ተከላካይ በመሆን አገልግሏል። ነገርግን በዘንድሮው ውድድር በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወልቂጤ ሥዩም ተስፋዬ እና ሁለገቡ ተስፋዬ ነጋሽን ማስፈረሙን ተከትሎ የቦታው ሦስተኛ ተመራጭ ተጫዋች ለመሆን ተገዷል።
ታድያ የሥዩም ተስፋዬ ከቀናት በፊት ከቡድኑ ጋር በስምምነት ለመለያየት መወሰኑ እና ተስፋዬ ነጋሽ በህመም መሰለፍ አለመቻሉ ለይበልጣል ሽባባው መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የመሰለፍን እድል ባገኘበት ጨዋታ ጥሩ ብቃቱን አሳይቷል።
እጅግ ታታሪ እና ያለውን ሁሉ ሜዳ ላይ ለመስጠት ዝግጁ የሆነው ተጫዋቹ ምንም እንኳን ቡድኑ በሰበታ ከተማ ቢረታም በግሉ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የነበረው ተሳትፎ ጥሩ የሚባል ነበር። በዚህ ሒደትም ሜዳ ላይ ያሳየው የነበረው ተነሳሽነትም አስደናቂ ነበር።
በተመሳሳይ በተሰረዘው የውድድር ዘመን አርባምንጭ ከተማን ለቆ በቅድሚያ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ቀጥሎም የመጀመሪያው ዝውውር አለመሳካቱን ተከትሎ ወደ ሀዋሳ ከተማ በማምራት በአዲሴ ካሳው ሀዋሳ ከተማ የመሐል ሜዳ ላይ አስደናቂ ጊዜያትን ማሳለፍ ችሏል።
ነገርግን ዓምና ሀዋሳ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ዋና ዳኛው ብሩክ የማነብርሀን በግንባሩ ለመማታት በመሞከሩ በቀይ ካርድ መውጣቱን ተከትሎ በድርጊቱ ለአንድ ዓመት ከማንኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ መታገዱ ይታወሳል። ይህን ቅጣት ከቀናት በፊት ያጠናቀቀው ተጫዋቹ ቡድኑ በፋሲል ከተማ በተረታበት ጨዋታ ዳግም በመጀመሪያ ተሰላፊነት በሀዋሳ ከተማ መለያ ተመልክተነዋል።
ጥሩ የሚባል የጨዋታ ጊዜ ያሳለፈው ቁመተ መለሎው አማካይ ከፍ ባለ ብርታት በሳጥን ሳጥን አማካይነት ዐምና ማሳየት የቻለውን አስደናቂ ብቃቱን ዘንድሮም መድገም የሚችል ከሆነ ለአሰልጣኝ ሙሉጌታ የአማካይ ክፍል ሌላ አማራጭን የሚፈጥር ይሆናል።
👉አቤል ማሞ እና ውሳኔዎቹ
ኢትዮጵያ ቡና መከተል ለሚፈልገው አጨዋወት ግብ ጠባቂዎች የሚወጡት ሚና እጅግ ላቅ ያለ ነው። ይህን ኃላፊነት ለመወጣት በሊጉ ከሚገኙ የተሻለ የራስ መተማመን እና በእግር ኳስን የመጫወት አቅምን መሰረት በማድረግ ቡድኑ ተክለማርያም ሻንቆ እና በረከት አማረን እንዲሁም ዘንድሮ ደግሞ ክለቡን በለቀቀው በረከት አማረ ምትክ አቤል ማሞን በስብስባቸው ውስጥ አካቷል።
በተሰረዘው የውድድር ዘመን ተክለማርያም ሻንቆ እና በረከት አማረን እያፈራረቀ ይጠቀም የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ ግን ከጥቂት ጨዋታዎች ውጪ በተቀዳሚነት ተክለማርያም ሻንቆን ሲጠቀም ተስተውሏል። ነገርግን በ10ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ጋር ሁለት አቻ በተለያየበት ጨዋታ ተክለማርያም ሻንቆ በተመለከተው የቀይ ካርድ ሳቢያ አቤል ማሞ ዳግም የመሰለፍ ዕድልን አግኝቷል።
ተጫዋቹ በግብ ጠባቂነት ክህሎቱ ብዙም ጥያቄ ባይነሳበትም ከልክ ባለፈ የራስ መተማመን በመነጨ የሚያሳልፋቸው አንዳንድ ውሳኔዎች ቡድኑን ለአደጋ ሲዳርጉ ይስተዋላል። ለአብነትም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በእግሩ የገባን ኳስ በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ለተያዙ የቡድን አጋሮቹ የሚያቀብልበት መንገድ እንዲሁም ጊዜያቸውን ባልጠበቁ የጨዋታ ቅፅበቶች የግብ ክልሉን ለቆ በወጣባቸው አጋጣሚዎች በእሱ ስህተት መነሻነት ቡድኑ ግብ ለማስተናገድ የቀረበባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ምስጋና ለሀዲያ ሆሳዕናዎች የዕለቱ ደካማ የአጨራረስ ብቃት እንጂ አቤል አስከፊ የጨዋታ ሳምንትን ለማሳለፍ በእጅጉ ተቃርቦ ነበር።
👉 ደስታውን በእንባ የገለፀው አምሳሉ ጥላሁን
ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከተማን 2-1 ሲረታ ለፋሲል ከነማ ሁለተኛዋን ግብ እጅግ አስደናቂ በሆነ መልኩ ማስቆጠር የቻለው የፋሲል ከነማው የግራ መስመር ተከላካይ አምሳሉ ጥላሁን ከግቧ በኋላ በዕንባ ታጅቦ ደስታውን ሲገልፅ ተስተውሏል።
ስለ ሁኔታው ከጨዋታው በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።
” ጎሉን አግብቼ ያለቀስኩት አራት ወንድሞቼ የምላቸው አብሮ አደጎቼን በሞት በማጣቴ ነው። ትንሽ የተወለድኩበት አካባቢ ባልተገባ ነገር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ወንድሞቼን በሞት በማጣቴ እነርሱን ለማሰብ ያለቀስኩት።” ሲል ሀሳቡን ገልጿል።
👉 ደምቆ የዋለው ወጣቱ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ
ጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል ሲዳማ ቡና ላይ ሲያሳካ የሜዳ ላይ ተጫዋቾች ካሳዩት ታታሪነት ባልተናነሰ የወጣቱ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ አበርክቶት የላቀ ድርሻን ይወስዳል።
ሰባት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ከተጋጣሚው የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች የተሰነዘረበት ወጣቱ ግብ ጠባቂ የሚቀመስ አልነበረም። ለተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ የመሰለፍ ዕድልን ያገኘው ወጣቱ አቡበከር አስደናቂ ብቃቱን ተጠቅሞ ያዳናቸው ኳሶች ቡድኑን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ አስችሏል። በዚህም አዲስ አበባ ላይ ቡድኑ በአዳማ ከተማ የመጀመሪያውን ሽንፈት ሲያስተናገድ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶ ተጠባባቂ የግብ ዘብ ያልነበረው ቡድኑን ዋጋ ያስከፈለበትን አጋጣሚ መካስ ችሏል።
👉 ወደ አቋሙ በመመለስ ላይ የሚገኘው
በረከት ደስታ
የሻሸመኔው ልጅ በረከት ደስታ ከደበዘዘ አቋሙ እየወጣ ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ እየሆነ መምጣቱን ያስመሰከረበትን ብቃት አሳይቷል። የቀድሞው የአዳማ ከተማ የመስመር አጥቂ ፋሲል ከነማን ከተቀላቀለ በኋላ ዘንድሮ በመጀመሪያ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ ዕድልን ቢያገኝም አጥጋቢ እንቅስቃሴ ባለማሳየቱ ወደ ተጠባባቂነት ወርዶ ነበር። ሆኖም ቡድኑ በጅማ የመጨረሻ ጨዋታው ድሬዳዋ ከተማን 2-0 ሲረታ ግብ ማስቆጠር የቻለው በረከት ዳግም በመጀመሪያ አሰላለፍ ተካቶ ትናንትም ፋሲልን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ በስሙ አስመዝግቧል። ከግቧ ውጪም ተጫዋቹ በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ውስጥ የነበረው ተሳትፎ በራስ መተማመኑን መልሶ በማግኘት ላይ መሆኑን የሚጠቁም ነበር። በረከት ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ የየጠውም አስተያየት ይህንን የሚጠቁም ነበር።
” የመጀመርያዎቹ አምስት ሳምንታት የነበረው እንቅስቃሴዬ ጥሩ ነበር። ያም ቢሆን ብዙ አጥጋቢ አልነበረም። ከዛ በኃላ ጅማ ላይ በነበረው ቆይታ አስቀድሞ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጬ ጨዋታዎችን በማየት ለምን እቀመጣለው በማለት እልህ ውስጥ ገብቼ አሁን ጥሩ ነገር እየሰራው እገኛለው።”
👉 ወላይታ ድቻን የታደገው መክብብ ደገፉ
የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ በነበረው የወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ትኩረትን የሳበው አንዱ ቅፅበት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማ ያገኘው የፍፁም ቅጣት ምት ነበር። ሆኖም ያለግብ በዘለቀው ጨዋታ ባህር ዳሮች ሙሉ ነጥብ አሳክተው ወጡ ሲባል የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉ የባዬ ገዛኸኝን ፍፁም ቅጣት ምት አድኖ ቡድኑንን ከሽንፈት ታድጓል።
ከሰዒድ ሀብታሙ ጋር በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እየተፈራረቀ በመሰለፍ ላይ የቆየው መክብብ ቡድኑ በሀዋሳ ከተማ 4-1 ከተሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ቀዳሚ ተመራጭ የመሆን ዕድሉን በእጁ አስገብቷል። በዚህ ሳምንት ለድቻ አንድ ነጥብ ማግኘት ምክንያት በመሆኑም በቀጣይ ጨዋታዎች የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ዕምነት እንደያዘ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
👉 ጉዳት የጨከነበት ፉዓድ ፈረጃ
በአዳማ ከተማ ይታይበት የነበረውን ብሩህ ተስፋ በሰበታ ማስቀጠል ለቻለው ፉዓድ 12ኛው ሳምንት መልካም ነገር ይዞ አልመጣም። በዘንድሮው ውድድር ጅማሮ ላይ የቡድኑን የማጥቃት ሂደት ከቀኝ መስመር እየተነሳ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከማገዝ ባለፈ በሁለተኛው ጨዋታ ግብ ማስቆጠርም ችሎ ነበር። ሰበታ እየተቀዛቀዘ በሄደባቸው ቀጣይ ጨዋታዎችም ተጨዋቹ በግሉ ጥሩ የጨዋታ ሂደትን ሲያሳልፍ ታይቷል።
የጅማው ውድድር ሲጀምር ግን በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ትልቅ ዕምነት የሚጣልበት ተጨዋች ከባድ ጊዜን ማሳለፍ ጀምሯል። 8ኛው ሳምንት ላይ ከባህር ዳሩ ሳሙኤል ተስፋዬ ጋር ተጋጭቶ ከባድ ጉዳት በማስተናገዱ ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች እንዲያመልጠውም ሆኗል። ታድያ በዚህ ሳምንት ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ ወደ ሜዳ ቢመለስም በጨዋታ ላይ የቆየው ግን ለ34 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። አማካዩ በድጋሚ ከባድ የሚመስል ጉዳት በማስተናገዱ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል። ፉዓድ እንደአጀማመሩ አብቦ ሊቀጥል የሚችልበት የውድድር ዓመት በተደጋጋሚ ጉዳት ሳቢያ ይበላሽበት ይሆን ?
© ሶከር ኢትዮጵያ