ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሁለት ሳምንት እረፍት በኋላ ባህር ዳር ላይ በ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቀጥሏል። የጨዋታ ሳምንቱን ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦችንም እንዲህ ዳሰናቸዋል።

👉 ዐፄዎቹ ልዩነታቸውን አስፍተዋል

በ12ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማን የገጠመው የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከቀጣይ ተፎካካሪዎቹ ነጥብ መጣል ጋር ተዳምሮ ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ማሳደግ ችሏል።

የኳስ ቁጥጥርን በመውሰድ ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲታትሩ የነበሩት ፋሲሎች በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ ለሀዋሳ ከተማ ፈታኝ ሆነው ተስተውለዋል። በ11ኛው እና በ44ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ እና አምሳሉ ጥላሁን ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦችም 2-0 እየመሩ ወደ መልበሻ ቤት ሊያመሩ ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ እየተመሩ የነበሩት ሀዋሳዎች ውጤቱን ለመቀልበስ በከፍተኛ ተነሳሽነት ቢንቀሳቀሱም ፋሲሎች ከጫና ነፃ ሆነው ኳስን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል። ሀዋሳዎች በ70ኛው ደቂቃ ወንድማገኝ ኃይሉ ባስቆጠራት ግብ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ቢሞክሩም በተቀሩት ደቂቃዎች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ሳይሰምርላቸው ቀርቷል።

አንደኛውን ዙር በበላይነት ማጠናቀቃቸውን ያረጋገጡት ፋሲል ከነማዎች እስካሁን ባደረጓቸው 11 ጨዋታዎች የጣሉት ነጥብ አምስት ብቻ ከመሆኑ በተጨማሪ ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች በድል በመደምደም በድንቅ ወቅታዊ አቋም ላይ መገኘታቸው ከተከታዮቻቸው የአቋም መዋዠቅ ጋር ተዳምሮ ከወዲሁ ስለ ቻምፒዮንነት ማሰብ እንዲጀምሩ ድፍረቱን የሚሰጣቸው ሆኗል። ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ከሆነ የተሟላ የሆነው ቡድን በተለያዩ ምክንያቶች ወሳኝ ተጫዋቾቹን የሚያጣ ከሆነ ክፍተቱን ለመድፈን ከሳምንት በኋላ በሚከፈተው የተጫዋቾች ዝውውር መስኮትም ስብስቡን የማጠናከር አጋጣሚን እንደሚፈጥርለት ይጠበቃል።

👉 ጅማ አባጅፋር በመጨረሻም አሸንፏል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በእስካሁኑ ጉዞ ማሸነፍ ተስኗቸው የቆዩት ጅማ አባ ጅፋሮች በ12ኛ የጨዋታ ሳምንት ግን በአዲሱ አሰልጣኛቸው ፀጋዬ ኪዳነማርያም እየተመሩ ሲዳማ ቡናን በሱራፌል ዐወል የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አሸንፈው በመውጣት የዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

እርሳቸው በሌሉበት ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከተጠቀመው ስብስብ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ ያደረጉት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በሁለቱም አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡና ብልጫ ቢወሰድባቸውም ጥብቅ በሆነ መከላከል መሪነታቸውን አስጠብቀው መውጣት ችለዋል።

በመሀል ሜዳ ላይ እና በጅማ አባ ጅፋር የሜዳ አጋማሽ ላይ ተገድቦ በተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጅማዎች ከኳስ ውጪ አብዛኛውን ደቂቃ ቢያሳልፉም በቁጥር በርከት ብለው በራሳቸው ሜዳ ለመከላከል ያሳዩት ትጋት እና ተነሳሽነት ግን የሚደነቅ ነበር።

ለረጅም ሳምንታት በሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ጅማ አባ ጅፋሮች ከሲዳማ ቡና ባሳኩት ሦስት ነጥብ ታግዘው ነጥባቸውን ወደ ሰባት በማሳደግ ከበላያቸው ከነበረው አዳማ ከተማ ጋር በነጥብ እና በግብ ልዩነት ተስተካክለው ለጊዜውም ቢሆን ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል። በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንትም መነሳሳት ላይ የሚገኘው ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን የሚገጥም ይሆናል።

👉 ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ድል ተመልሷል

ከሰሞነኛ ውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ ከፍ ባለ ጫና ውስጥ ይገኙ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የራስ መተማመናቸውን ሊያሳድግ የሚችል የ4-2 ድል አዳማ ከተማ ላይ አስመዝግበው ዳግም ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል።

ግቦቹ ከተገኙበት መንገድ በዘለለ ቡድኑ 3-0 ከመራ በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች በተጫዋቾቹ ላይ ይነበብ በነበረው የትኩረት ማጣት ሳቢያ በአዳማ ከተማ ሁለት ግብ ማስተናገዳቸው እና የመጨረሻዋ የአማኑኤል ግብ እስክትገኝ ድረስ አዳማ ከተማዎች በጊዮርጊስ 3-2 የበላይነት ይጓዝ የነበረውን ውጤት ለመቀልበስ ከፍተኛ ጫና መፍጠራቸውን ለተመለከተ አሁንም ቡድኑ ወደ ትክክለኛ አቋሙ የመመለሱ ነገሩ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ የተመለከትንበት ጨዋታ ነበር።

በተቃራኒው በጫና ውስጥ ለሰነበተው ቡድኑ ከጫና እንዲላቀቅ በየትኛውም መንገድ የሚገኝ ድል ለአሰልጣኝ ቡድኑ አባላት የመተንፈሻ ጊዜ ከማስገኘቱ በዘለለ የተጫዋቾችን የማሸነፍ ሥነልቦናን በማንሳት ረገድ ከፍ ያለ ድርሻን የመወጣቱ ነገር ቢታመንበትም ቡድኑ ይህን ድል እንደመነሻ በመውሰድ ለዋንጫ የሚያደርገውን ፉክክር ዳግም ያነቃቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ከቀናት በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13ኛ ሳምንት መርሐግብር ለትላልቅ ቡድኖች ፈተና በመሆን የሚታወቀውን ወልቂጤ ከተማን የሚገጥም ይሆናል።

👉ሰበታ ከተማ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘውን አዳማ ከተማን በመርታት ከድል የታረቁት ሰበታ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ተቸግረውም ቢሆን ወልቂጤ ከተማን በመርታት ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

ክፍት የሆነ እንቅስቃሴን ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወልቂጤ ከተማዎች በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በንፅፅር የተሻሉ ነበሩ። ወልቂጤ ከተማዎች ከጨዋታ ውጪ በሚል የተሻሩባቸውን አጨቃጫቂ ኳሶች ጨምሮ ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ሰበታ ከተማዎች በ69ኛው ደቂቃ መሳይ ጳውሎስ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ ቋሚ የመለሰበትን ኳስ ከግቡ በቅርብ ርቀት የነበረው ፍፁም ገ/ማርያም በቀላሉ አስቆጥሮ ቡድኑን ለተከታታይ ድል አብቅቷል።

በዚህም ውጤት መሠረት ሰበታ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ አስራ ሦስት በማሳደግ በጥቂት ሳምታት ውስጥ ይገኙበት ከነበረው የወራጅ ቀጠና ስጋት ተላቀው ስምንተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅተዋል።

👉 ተነሳሽነት የጎደለው ባህር ዳር ከተማ

ባህርዳር ከተማ ወደ ከተማው በመጣው የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ከሌሎች ቡድኖች በተሻለ የ18 ቀናት ዕረፍት በኋላ ወደ ውድድር ከተመለሱት ወላይታ ድቻዎች ጋር ያለ ግብ አቻ በመለያየት በሰንጠረዡ አናት ከሚገኙ ቡድኖች ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያስችለውን ዕድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ባህርዳር ከተማዎች ከወገብ በላይ የሚገኙትን ፈጣን ተጫዋቾችን በመጠቀም ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ካደረጉት ጥረት ውጪ ኳሱን ለአመዛኙ የጨዋታ ክፍለጊዜ በቁጥጥራቸው ስር ከማዋል በዘለለ ይህ ነው የሚባሉ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ምንም እንኳን የጣና ሞገዶቹ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የቀድሞው የወላይታ ድቻ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ የመታው ኳስ በድቻው ግብጠባቂ መክብብ ደገፉ አስደናቂ ብቃት ሊድንበት ከመቻሉ በዘለለ ባህርዳር ከተማዎች በ90 ደቂቃው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ይህ ነው የሚባል የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ቡድኑ ባለፉት ሳምንታት ጨዋታዎቹ ከእንቅስቃሴ የመውጣት እና የተነሳሽነት ችግር በተደጋጋሚ ሲስተዋልበት ከመቆየቱ አንፃር ውድድሩ ወደ ባህር ዳር መሄዱ ይህን ችግር በመጠኑ ቀርፎ እንዲገባ ያስችለዋል ተብሎ ቢጠበቅም በድቻው ጨዋታ ላይ የነበረው የቡድኑ እንቅስቃሴ ይህን የሚነግር አልነበረም።

ባህር ዳር በዚህ ሳምንት አራፊ ቡድን እንደመሆኑ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እና ረዳቶቻቸው ተጠባቂነቱን የመጠነ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የማይገኘውን ቡድን የማሻሻል እፎይታን ያገኛሉ።

👉 ኢትዮጵያ ቡና እና ያልተሻገረው ችግር

በ12ኛ የጨዋታ ሳምንት በሰንጠረዡ አናት ፋሲል ከተማን ተከትለው በሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕናን ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው በጉልህ ያስተዋልነው ጉዳይ በትዕግስት ኳስን ተቆጣጥሮ ማጥቃትን የሚሻው የካሣዬው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደውን እና የጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ባለቤት የሆነውን ሀዲያ ሆሳዕናን የመከላከል አወቃቀር ለመስበር እጅጉን ተቸግሮ ተስተውሏል። የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የጨዋታ እንቅስቃሴ ቡድኑ በአዲስአበባ ስታዲየም በሀዋሳ ከተማ ከተረታበት ጨዋታ ጋር በእጅጉ የሚመሳሰልም ነበር።

በእርግጥ አብዛኞቹ ቡድኖች እንደ ኢትዮጵያ ቡና ዓይነት ቡድኖችን ሲገጥሙ ወደ ራሳቸው ሜዳ አድልተው በጥንቃቄ መከላከል ተቀዳሚ ምርጫቸው እንደሚሆን የሚታወቅ ቢሆንም በሀዲያ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ከተማ ደረጃ ለዘጠና ደቂቃ በላቀ የትጋት እና ትኩረት ደረጃ የሚከላከሉ ቡድኖች ሲሆኑ ደግሞ ለተጋጣሚ ምን ያህል ጨዋታውን ፈታኝ እንደሚያደርግበት ኢትዮጵያ ቡና ሁለቱን ቡድኖች በገጠመበት ጨዋታ ማስተዋል ችለናል።

ኢትዮጵያ ቡና መሰል ተጋጣሚዎች ሲገጥሙት አስከፍቶ የግብ እድሎችን ለመፍጠር አሁን ድረስ እንደተቸገረ ቀጥሏል። ቡናማዎቹ መሰል ተጋጣሚዎችን ለማስከፈት በሚቸገሩባቸው ጨዋታዎች ኳሶች በመካከለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተገድበው ኳሶቹን ከመቀባበል በዘለለ ቀዳዳዎችን ለማስከፈት የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ አይደለም።

ከመሰል ተጋጣሚዎች ጋር ቡድኑ በፍጥነት ኳሶቹን ከአንዱ የሜዳው ወገን ወደ ሌላው በመቀያየር የተጋጣሚን የመከላከል አደረጃጀት ከአንዱ የሜዳ ጠርዝ ወደ ሌላው በመገለባበጥ ክፍተቶችን ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት ኳሶቹን በፍጥነት መቀባበል ባለመቻላቸው ተጋጣሚዎቻቸውን ቅርፃቸውን ዳግም በቀላሉ እንዲያዝ ሲያስችላቸው ይስተዋላል። በተጨማሪም በመሰል የግብ አጋጣሚዎች እጅግ ጥቂት በሚሆኑባቸው ጨዋታዎች የቡድኑ ተጫዋቾች አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት በመቀየር ረገድ ያለባቸው የስልነት ጉድለት ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍል ተስተውሏል።

ቡድኑ በተለይ በሁለተኛው ዙር እያንዳንዱ ጨዋታ ላይ የሚገኙ ነጥቦች ዋጋቸው ከፍ እያለ በሚመጣበት የውድድሩ ሂደት ቡናን የሚገጥሙ ቡድኖች ፍፁም መከላከልን ምርጫቸው አድርገው መምጣታቸው የሚጠበቅ እንደመሆኑ ቡድኑ በተፎካካሪነት እንዲዘልቅ ይህን ሂደት በአፋጣኝ ማሻሻል የግድ ይለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ