“…አባቴ ለአሰበበት ነገር በጣም የሚታገል ሰው ነው” አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ

ከደደቢት ተስፋ ቡድን የተገኘውና አሁን በሰበታ ከተማ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ የእግርኳስ ህይወቱን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ አበባ ከተማ ካሳንችስ 28 ሜዳ አካባቢ ተወልዶ አድጓል። ብዙ ባልተለመደ ሁኔታ ወላጅ አባቱ “ልጄ ትልቅ እግርኳስ ተጫዋች ይሆንልኝ ዘንድ ምኞቴ ነው።” በማለት ገና ከስምንት ዓመቱ ጀምሮ እግርኳስ ተጫዋች እንዲሆን ከኳስ ጋር እንዲተዋወቅ አድርገውታል። ከስምንት ዓመቱ ጀምሮ እግርኳስ ተጫዋች እንዲሆን የአባቱ ክትትል ያልተለየው አብዱልሀፊዝ ራዕይ በሚባል የታዳጊ ቡድን በፕሮጀክት ደረጃ ሲጫወት ቆይቶ በ2007 ነበር የደደቢት ከ17 ዓመት በታች ቡድንን በመቀላቀል እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ለአምስት ዓመታት ሲጫወት የቆየው።

ወጣቱ አማካይ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሰበታ ከተማን በመቀላቀል መልካም የሚባል የውድድር ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች የመሰለፍ እድል ማግኘት ባይችልም ቀስ በቀስ ወደ አሰላለፍ በመግባት በተለይም ጅማ ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ በመጫወት ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል። ከእድሜው ለጋነት አንፃር እጅግ መረጋጋት የሚታይበት አብዱልሀፊዝ የቴክኒክ ክህሎቱ እና የኳስ የማቀበል ችሎታው በልምድ እየዳበረ ሲሄድ እንደ ቡድን አጋሮቹ መስዑድ እና ዳዊት ወደፊት ትልቅ ደረጃ መጫወት እንደሚችል ተስፋ የሚጣልበት ነው።

አማካዩ ስለ እግርኳስ ህይወቱ እና ከአባቱ ጋር ስላለው ልዩ ቁርኝት ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቶናል።

እግርኳስ ተጫዋች የመሆኑ ምክንያት

ለእኔ እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን ምክንያቴ አባቴ ነው። እኔ ኳስ ተጫዋች እንድሆን ዓላማ ነበረው። ከስምንት ዓመቴ ጀምሮ ነው እንድጫወት ይፈልግ የነበረው። አባቴ ከሌሎች ቤተሰቦች በብዙ መልኩ ይለያል። ልጆቹ በአንድ ነገር ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ነገር ላይ ትኩረት እንድናደርግ ይፈልጋል። በትምህርቱ ረዥም ርቀት እንድንሄድ ቢፈልግም ተጨማሪ አንድ ነገር ጎን ለጎን እንድንይዝ ይፈልጋል። ይሄን ሁሉም ልጆቹ ላይ አድርጓል። እኔን ደግሞ ያለኝን ነገር ተረድቶ ነበር መሰለኝ ኳስ ተጫዋች እንድሆን ብዙ እቅዶች ነበሩት አንዱን አሳክቷል።

በደደቢት ስለነበረው ቆይታ

ከ2007 ጀምሮ ከተስፋ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ለአምስት መጨወት ችያለው። መሀል ላይ ጉዳት አጋጥሞኝ ተቸግሬ ነበር። በኃላ ከጉዳቴ አገግሜ መጫወት ችያለው። ደደቢት ፕሪምየር ሊጉ በነበረበት ጊዜም አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬ ቡድኑ እስከወረደበት ጊዜ ድረስ አምኖብኝ አጫውቶኛል። በከፍተኛ ሊግም ለቡድኑን ሳገለግል ቆይቻው።

የእስካሁን የሰበታ ቆይታው

በሰበታ ያለኝ ቆይታ ዩኒቨርስቲ የመግባት ያህል ነው የምቆጥረው። ምክንያቱም በቦታዬ የሚጫወቱት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን የተጫወቱ ተጫዋቾች መሐል መጫወት ለኔ ጥሩ ትምህርት ቤት የገባው ያህል ነው የሚሰማኝ። ከኳስ ጋር የተገናኘውንም ሆነ ብስለት ላይ ያለውንም ከእነርሱ ጋር መጫወት ልምድ እያገኘሁ ነው። ለእኔ ይሄ ጥሩ አጋጣሚ ነው።

ስለ አባቱ

አባቴ ላሰበበት ነገር በጣም የሚታገል ሰው ነው። ያሰበውን እስኪያሳካ እንቅልፍ የማይተኛ ሰው ነው። በኔ ጉዳይም ያለመው ያቀደው ጉዳይ ስለነበር እስከ ስነ ምግብ ወርዶ አመጋገቤን ያስተካክል የነበረ፣ የህክምና ባለሙያ ሳይሆን እግሬን እስከማሸት የደረሰ ብዙ ዋጋ የከፈለልኝ አባት ነው። ብቻ በሁሉም ነገር ብቁ የሆነ ጠንካራ አባት ነው።

የአቱ አርዓያነት ለሌሎች አባቶች

በእግርኳሱ እንዲህ ያለ አባት አልተለመደም። ይህ ከነፃነት በላይ ነው። ሂድ ኳስ ተጫዋች ሁን ከሚለው በላይ ነው። ይሄን ያህል ዓመት አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እያደረገ እኔን እዚህ ደረጃ ማድረስ ብዙ ዋጋ ከፍሏል። ይህ ነገር ብዙ አልተለመደም። ልጁን ከትምህርት ውጭ ሁለተኛ ነገር ሙያ ሊኖረው ይገባል ብሎ ማሰቡ አስገራሚ ነው። ሁሉም ወላጅ ነፃነቱን ሰጥቶ ትንሽ ክትትል ቢያደርግ በጣም ጥሩ ነው እላለው።

አባትህ ለከፈለው ዋጋ ያለው ምላሽ

እኔንጃ! እርሱ ለኔ ትልቁ ክፍያ ብሎ የሚያስበው እርሱ የሚያስበው ደረጃ ላይ መድረስን ነው። እርሱ የሚያስበው ደረጃ ደግሞ እዚህ ሀገር በመጫወት የሚገደብ አይደለም። አላህ ቢያደርሰኝ እርሱ የሚያስበው ቦታ የምደርስ ከሆነ በጣም ነው ደስተኛ የምሆነው። እርሱም የሚያስበው እንደዛ ነው። ብዙ የቤተሰብ አቅም፣ የገንዘብ ችግር የለብንም። ለእርሱ ያሰበበት ደረጃ ደርሼ ቢያየኝ ለእርሱ ትልቁ ክፍያ ይሄ ነው።

ቀጣይ ሀሳብ

አላህ ካለ በእግርኳሱ ሰበታ ላይ የሚታይ በጎል ማግባት የጎል ዕድል በመፍጠር ተፅዕኖ ማሳደር እፈልጋለሁ። ቀጥሎ በብሔራዊ ቡድን ሀገሬን ማገልገል፤ ከዛ ባለፈ ውጭ ወጥቶ የመጫወት ፍላጎት ሀሳቡ ነበረኝ። ከዚህ በፊት ጤነኛ በሆንኩበት ሰዓት ዕድሎች ነበሩ፤ በጉዳት ሳይሳካ ቀርቷል። አሁን እርሱን አሳክቼ እንደነ ሽመልስ እንደ ቢንያም የመሆን ሀሳብ አለኝ።

በመጨረሻ

ፈጣሪን አመሰግናለው። ሲቀጥል አባቴ ሁሌም ከጎኔ አለ። ቤተሰቦቼን፣ እናቴን፣ ከ ቢ ጀምሮ ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች፣ ደደቢት እያለሁ ፕሪምየር ሊግ እንድጫወት አምኖ ዕድል የሰጠኝ አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬን በጣም አመሰግናለሁ። አሁንም ኢንስትራክተር አብርሀም ስር ዕድል ሰጥቶ እያጫወተኝ ስለሆነ እርሱንም አመሰግናለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ