ቅድመ ዳሳሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የነገው ሁለተኛ ጨዋታ ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት ይሆናል።

ወልቂጤ ከተማ በሰበታ ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዶ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል። ቡድኑ ጠንካራ አቋሙን ይዞ ባለመዝለቁም ወደ ላይ ከፍ ማለት የሚልባቸውን ዕድሎች በየጣልቃው በሚገጥሙት ሽንፈቶች እያጣ ለ13ኛው ሳምንት በቅቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች መልስ በአዳማ ላይ ድል አስመዝግቦ ነው የሚቀርበው። ቡድኑ ባስመዘገበው ውጤት ወደ ሦስተኝነት ከፍ ሲል ነገም በኢትዮጵያ ቡና ውጤት ላይ ተመርኩዞ ሁለተኝነትን የመያዝ ዕድሉም ይኖረዋል።

በነገው ጨዋታ ለአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ትልቁ ፈተና የዋነኛ ተጨዋቾቻቸው አለመድረስ ነው። ከእነዚህ ውስጥ የመሀል ተከላካዩ ዳግም ንጉሴ መሰለፍ አጠራጣሪ ሲሆን ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰውም ከሰበታው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት የሦስት ጨዋታዎች ቅጣቱን ነገ ይጀምራል። ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ ቀዳሚ ተመራጮች የሆኑት ፍሬው ሰለሞን ፣ ሀብታመ ሸዋለም እና ተስፋዬ ነጋሽ እንዲሁም በሰበታው ጨዋታ የቡድኑን የቀኝ መስመር ተከላካይ ቤታ ክፍተት በጥሩ ብቃት የሸፈነው ይበልጣል ሽባባው እና አዳነ በላይም ከነገው የወልቂጤ ስብስብ ውጪ መሆናቸውን ሰምተናል።

ወልቂጤ ውድድሩ ሲጀምር የነበረው የተሟላ ስብስብ በተለይም ከወገብ በታች ባለው መዋቅሩ ላይ በዚህ መልኩ መሳሳቱ በጥንካሬው ለሚነሳው የኋላ ክፍሉ መከፈት አስተዋፅዖ ሊኖረው ይችላል። በዳኝነት ስህተት ሳቢያ በሰበታው ጨዋታ ነጥብ ማጣቱን ተከትሎም ተከታታይ ሽንፈቶች ላለማስተናገድ ጊዮርጊስን የሚገጥምበትን ጨዋታ በጫና ውስጥ እንዲከውን ሊያደርገው የሚችል ጉዳይ ነው። ቡድኑ ከዚህ ቀደም በጉድለቶች ውስጥ ሆኖም ራሱን እንደተጋጣሚው ሁኔታ በመቀያየር ጥሩ ፉክክር ሲያደርግ መመልከታችን ግን ነገም አንዳች ነገር እንድንጠብቅ የሚደርገን ይሆናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተጋጣሚው በተቃረነ ሁኔታ ሙሉ ስብስቡ ጤንነት ላይ ይገኛል። ከዚህ ባለፈም በባህር ዳሩ ጨዋታ የቀይ ካርድ ተመልክቶ የነበረው አስቻለው ታመነም ነገ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል። ጊዮርጊስ ከግብ ርቆ ሰንብቶ አዳማ ላይ አራት ጎሎችን በማስቆጠር ማሸነፉ ቡድኑ ፊት ላይ የነበረውን ጥንካሬ መልሶ ለማግኘት እንደመነሳሻ የሚሆነው ነጥብ ነው። በተለይም አማራጮችን የጨረሰው እና በአስገዳጅ ለውጥ ሊሸፈን የሚችለው የተጋጣሚውን የቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ከግብ ጋር በታረቀው አማኑኤል ገብረሚካኤል ብቃት ታግዞ የመጠቀም ዕድሉ የሰፋ ነው።

በሌላ ጎኑ የአሰልጣኝ ማሂር ዴቫድስ ቡድን በአዳማው ጨዋታ ማብቂያ ላይ ከታየበት መዘናጋት ግብ ማስተናገዱ ከነገው ጨዋታ በፊት አስተካክሎት ለመምጣት የሚያስበው ድክመቱ እንደሆነ ይታመናል። የአስቻለው ወደ ሜዳ መመለስም መሰል ችግሮችን ሊቀርፍ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ከዚህ ውጪ ፊት ላይ በርከት ያሉ አጥቂዎችን የመጠቀሙን ሂደት ለአቤል እንዳለ ዕድሉን በመስጠት ባደረገው ጨዋታ ውጤት ማስመዝገቡ ቡድኑ ከጌታነህ ከበደ ውጪ በሁለቱ መስመሮች አማኑኤል እና አቤል ያለውን በማሰለፍ በተሻለ የአማካይ ተጨዋቾች ስብስብ ጨዋታውን እንደሚጀምር ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በተሰረዘው የውድድር ዓመት ሁለት ጊዜ ተገናኝተው አንድጊዜ ያለግብ ሲለያዩ በሌላኛው ወልቂጤ 1-0 መርታት ችሎ ነበር። የነገው ጨዋታቸው ግን በሊጉ የመጀመሪያ ግንኙነት ሆኖ ይመዘገባል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ዮሐንስ በዛብህ

መሀመድ ሻፊ – ቶማስ ስምረቱ – ተስፋዬ መላኩ – ረመዳን የሱፍ

ያሬድ ታደሰ– አሳሪ አልመሀዲ – አብዱልከሪም ወርቁ

አቡበከር ሳኒ – ሄኖክ አየለ – አሜ መሀመድ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – አብዱልከሪም መሀመድ

የአብስራ ተስፋዬ – ናትናኤል ዘለቀ

አቤል ያለው – አቤል እንዳለ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

ጌታነህ ከበደ


© ሶከር ኢትዮጵያ