ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የ13ኛውን ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ የተመለኩቱ ጉዳዮችን እንዲህ አንስተናል።

ሀዋሳ ከተማ ላይ ባሳካው ድል ማንሰራራት የመጀመር ዕድል የነበረው አዳማ ከተማ በደረሱበት ተከታታይ ሽንፈቶች ወደ ሊጉ ግርጌ ወርዷል። ነገስ ‘ከአስከፊው ጉዞ ለማገገም ከጠንካራው ተጋጣሚ ነጥብ ያገኝ ይሆን ?’ የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ሆኗል።

እንዳለው ስብስብ እና እንደሚገኝበት ሁኔታ ጥብቅ መከላከልን ምርጫው ሲያደርግ የማይታየው አዳማ ከተማ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታም በራሱ መንገድ ጨዋታውን ለማስኬድ መሞከሩ የሚቀር አይመስልም። ይህን ለማድረግ የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ግቦችን በቶሎ ለማግኘት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን በተለይ በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ የሚያደርጋቸውን ተደጋጋሚ ለውጦች ተከትሎ የሚታዩ ግለሰባዊ ስህተቶች ይበልጥ ችግር ውስጥ ሊከቱት የሚችሉበት ዕድል ይኖራል።

እርግጥ ነው እንደ እነፍሰሀ ቶማስ እና አብዲሳ ጀማል ዓይነት የቡድኑ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያዎች በተመሳሳይ ስህተት የማያጣውን የቡናን የኋላ ክፍል ስህተቶች የመጠቀም አቅሙ አላቸው። ቡድኑ ምንም እንኳን ሽንፈት ቢገጥመውም በጊዮርጊሱ ጨዋታ ከኋላ ተነስቶ ግቦችን ማስቆጠሩም የሚነግረንም በቀላሉ ሊገመት እንደማይገባ ነው። ነገር ግን በራሱ ሜዳ ላይ የሚሰራቸው ስህተቶች ካልታረሙ ግብ ማስቆጠሩ ብቻውን ጨዋታውን ለተመልካች አዝናኝ ከማድረግ ባለፈ አብዝቶ የሚፈልገውን ነጥብ ይዞለት ላይመጣ ይችላል።

ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማው የ 5-0 ድል በኋላ ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ግብ ማስቆጠር ተስኖት ከበላዩ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ልዩነቱን እንዲያሰፋ ዕድሉን ከፍቷል። ነገ ደግሞ የሁለትኝነት ደረጃውንም እንዳያጣ ጨዋታውን ማሸነፍ የግድ ይለዋል።

ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ከባድ የተከላካይ ክፍል ካለው ቡድን ጋር ካደረገው ጨዋታ መልስ በሊጉ ሁለተኛውን በርካታ ግብ ካስተናገደ ቡድን ጋር መገናኘቱ መጠነኛ እፎይታ የሚሰጠው ይመስላል። ቡድኑ በደካማ የመከላከል አደረጃጀት ውስጥ ሆነው ተጋጣሚዎች ትኩረታቸው በሚቀንስባቸው ወቅቶች ላይ ምን ማድረስ እንደሚችል የሲዳማውን ጨዋታ መመልከት በቂ ይሆናል። ነገም የሜዳውን ስፋት አብዝተው በሚጠቀሙት የመስመር አጥቂዎቹ እገዛ ተጋጣሚውን የመበተን እንዲሁም በርካታ ቅብብሎቹን በሚከውኑት አማካዮቹ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች በግብ ፊት ለመድረስ ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ውስጥ ሁነኛ ተሳታፊ በሆነው አስራት ቱንጆ የሚረዳው የግራው ወገን የቡድኑ ክፍል ባለፈው ጨዋታ ከሀብታሙ ታደሰ አለመሰለፍ ጋር ተያይዞ አመርቂ ያልነበረ በመሆኑ በቦታው ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል። በመከላከሉ ረገድ ስንመለከተው ግን ለሁለተኛ ጊዜ ግብ ሳያስተናግድ መውጣቱ እንዳለ ሆኖ ከሀዲያ ጋር የታዩበት በርካታ ስህተቶች ከተደገሙ ዳግም ግብ አያስተናግድም ብሎ ለመናገር ከባድ ይሆናል። በዚህ ረገድ የቡድኑን ዕምነት ሜዳ ላይ ከመተግበር ባለፈ በፈታኝ ቅፅበቶች ትክክለኛውን ውሳኔ ማሳለፍ ከቡና የኋላ ክፍል ተሰላፊዎች የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች 36 ጊዜ ተገናኝተው ቡና 20 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ 7 ጊዜ አዳማ አሸንፏል። 9 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

– 95 ጎሎች በተስተናገዱበት የሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 63፤ አዳማ 32 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ታሪክ ጌትነት

ታፈሰ ሰርካ – ደስታ ጊቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – እዮብ ማቲያስ

ሙጃይድ መሀመድ – ደሳለኝ ደባሽ

ፀጋዬ ባልቻ – በቃሉ ገነነ – ፍሰሀ ቶማስ

አብዲሳ ጀማል

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አስራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – ረመዳን ናስር – ዊሊያም ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – አቤል ከበደ


© ሶከር ኢትዮጵያ