ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ጌዲኦ ዲላ የንግድ ባንክን ያለመሸነፍ ጉዞ ገታ

የእጅጋየው ጥላሁን ብቸኛ ጎል ጌዲኦ ዲላን አሸናፊ ስታደርግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ቀምሷል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአስራ ሁለተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን አራተኛ ጨዋታ ከረፋዱ ጨዋታ በመቀጠል ከሰዓት 10፡00 ላይ በመሪው ንግድ ባንክ እና ጌዲኦ ዲላ መካከል ተከናውኗል፡፡ በሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ብርሁ ፉክክር ባየንበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በጌዲኦ ዲላ እጅጉን የተፈተኑበት እና ከወትሮው ጥንካሬያቸው ደከም ብለው የታዩበት እንደነበር በሜዳ ላይ በታየው እንቅስቃሴ መመልከት ችለናል፡፡

በመጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ንግድ ባንክ ተሽሎ መታየት ቢችልም ደካማ በአጨራረስ ችግር የተገኙትን መልካም አጋጣሚዎች እንዲጠቀሙ አላስቻላቸውም፡፡ 8ኛው ደቂቃ ላይ እመቤት አዲሱ ከቀኝ በኩል ያሻገረችሁን ኳስ አረጋሽ ካልሳ ጋር ደርሶ ተጫዋቿም በቀላሉ አስቆጠረችው ሲባል ወደ ውጪ የሰደደችበት ቅፅበት ለማመን የሚከብድ የመጀመሪያ የጨዋታው ሙከራ ሆናለች፡፡ በግራ አቅጣጫ ተሰልፋ ወደ ጌዲኦ ዲላ የግብ ክልል ሰብሮ ለመግባት ጥረት ስታደርግ የነበረችሁ አረጋሽ ካልሳ ከቡድን አጋሮቿ የምታገኛቸው እገዛዎች የተሳኩ ባለመሆናቸው ጥረቶቿ ብኩን ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡

በመከላከሉ ጠንካራ የነበሩት ጌዲኦ ዲላዎች ለደቂቃዎች ለንግድ ባንክ እጃቸውን መስጠት ቢችሉም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ቅርፅ በመግባት በመልሶ ማጥቃት በረጃጅም ኳሶች ወደ ንግድ ባንክ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል፡፡ በተለይ እፀገነት ግርማ ከእግሯ ሲነሱ የነበሩ ኳሶች ሊጠቀም የሚችሉ ሁነኛ አጥቂዎች በቡድኑ አለመኖሩ እንጂ አጋጣሚዎቹን የሚጠቀም ተጫዋች ቢኖር ኖሮ ምናልባት ግብ በቻሉ ነበር፡፡

25ኛው ደቂቃ ህይወት ደንጊሶ ከርቀት አክርራ ስትመታ መስከረም መንግስቱ ስታድነው ረሂማ ዘርጋው በድጋሚ አግኝታው ንግድ ባንክ መሪ አደረገች ሲባል የግቡ የቀኝ ቋሚ ብረት መልሶባታል፡፡ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ጭማሪ ደቂቃ ላይ የጌዲኦ ዲላዋ አጥቂ ይታገሱ ተገኝወርቅ የሚገርም አጋጣሚን አግኝታ ስታዋለች፡፡

ከእረፍት መልስ በይበልጥ የጌዲኦ ዲላ ታታሪነት የታየበት እና ኢትዮጽያ ንግድ ባንኮች በመስመር አጨዋወት በጌዲኦ ዲላ ብልጫን ለመወስድ ጥረቶች ያደረጉበት ነበር፡፡ በተለይ በተደጋጋሚ በጌዲኦ ዲላ የተፈተኑት አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው በተደጋጋሚ በቡድናቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ አለመሆናቸው በሚያሳዩት እንቅስቃሴ ማስተዋል ችለናል፡፡ ብዙነሽ ሲሳይ ተቀይራ በታሪኳ ዴቢሶ ከገባች በኃላ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል የምትልካቸው ኳሶች አስፈሪ ይመስሉ የነበሩ ቢሆንም የንግድ ባንክ የአጥቂ ክፍል መዳከም የኃላ ኃላ ዋጋ እንዲከፍሉ አስገድዷቸዋል፡፡

80ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን በቀኝ መስመር ላይ የነበረችው ትዝታ ፈጠነ በአግባቡ ተቆጣጥራው ወደ ሳጥን በመግባት በቀጥታ ስትመታው የግቡ ቋሚ ብረት መልሶባት በድጋሚ እፀገነት ግርማ ስትመታው ኳሷ አቅጣጫውን ቀይራ ተቀይራ ከገባች ሰባት ደቂቃዎች ብቻ ሜዳ ላይ የቆየችው እጅጋየሁ ጥላሁን ጨረፍ አድርጋ በማስቆጠር ጌዲኦ ዲላን መሪ አድርጋለች፡፡ ጎሏ ከተቆጠረች በኃላ የጌዲኦ ዲላው አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የነበረው የደስታ አገላለፅ የነበሩትን ተመልካቾች ፈገግ ያሰኘ እና ያዝናና ነበር፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ባንኮች ሙሉ ሀይላቸውን በመጠቀም አቻ ለመሆን የጣሩ ቢሆንም የመረጋጋት ችግር ይንፀባረቅባቸው ስለነበር በጌዲኦ ዲላ የዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የጌዲኦ ዲላዋን ግብ ጠባቂ መስከረም መንግስቱን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ