አዳማ ከተማ አዲስ አሠልጣኝ ሊሾም ነው

በዛሬው ዕለት ከአሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል ጋር የተለያዩት አዳማ ከተማዎች በቦታው አዲስ አሠልጣኝ ለመሾም ተቃርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ላይ ደካማ ጉዞን እያደረገ የሚገኘው እና በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጠው አዳማ ከተማ በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ ቡናን ሲመራ ከቆየ በኃላ ከእረፍት መልስ በተቆጠሩበት አራት ጎሎች 4ለ1 ለመሸነፍ ተገዷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የክለቡ አሰልጣኝ አስቻለው ኃይለሚካኤል በገዛ ፍቃዳቸው ከክለቡ አሰልጣኝነት መሰናበታቸውን የገለፁ ሲሆን ክለቡ ከአሰልጣኙ መለያየት በኃላ በምትካቸው አዲስ አሠልጣኝ ለማምጣት ንግግር ጀምሯል። ሶከር ኢትዮጵያ ከምንጮቿ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ አዲስ ፕሬዝዳንት ያገኙት አዳማዎች አሠልጣኝ አዲሴ ካሳን ለመቅጠር መቃረባቸው ታውቋል።

የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ፣ ደቡብ ፖሊስ፣ ወልቂጤ ከተማ እንዲሁም ከ2011 እስከ ተሰረዘው የዓምና የውድድር ዓመት አጋማሽ ድረስ በድጋሚ የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ አዲሴ ከክለቡ የበላይ አመራሮች ጋር በመሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መነጋገራቸው ተሰምቷል። አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስም ቀጣዩ የክለቡ ዋና አሠልጣኝ ለመሆን መቃረባቸውን ለማረጋገጥ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ