ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎች

በአስራ ሁለተኛ ሳምንት ላይ የተመረኮዙ ዕውነታዎች፣ ቁጥሮች እና የዲሲፕሊን መረጃዎች እንዲህ አጠናቅረናል።

– በዚህ ሳምንት በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች 11 ጎሎች ብቻ ተቆጥረዋል። ይህም ባለፈው ሳምንት ከተቆጠረው በሦስት ያነሰ ሲሆን ከዘጠነኛው ሳምንት በመቀጠል ዝቅተኛ ጎል የተቆጠረበት የጨዋታ ሳምንት ሆኗል።

– ከ11 ጎሎት መካከል አምስቱ በመጀመርያ አጋማሽ ሲቆጠሩ ስድስቱ ጎሎች ከዕረፍት በኋላ ተቆጥረዋል።

– የቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበት ከፍተኛውን ቁጥር ሲይዝ ሁለት ጨዋታዎች ያለ ጎል ተጠናቀዋል።

– ቅዱስ ጊዮርገስ አራት ጎሎችን በተጋጣሚው አዳማ ከተማ ላይ በማስቆጠር የሳምንቱን ከፍተኛ የጎል ማስቆጠር ቁጥር አስመዝግቧል።

– ከተቆጠሩት ጎሎች መካከል (1) ሱራፌል ዐወል በፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥር አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቅጣት ምት የተነሳ ኳስ ተጠቅሞ አስቆጥሯል። ፍፁም ገብረማርያም ደግሞ መነሻው ከማዕዘን ምት የሆነ ኳስ ከመረብ አሳርፏል። ሌሎቹ ጎሎች በክፍት ጨዋታ የተቆጠሩ ናቸው።

– አምሳሉ ጥላሁን ከሳጥን ውጪ መትቶ ያስቆጠረ ብቸኛው ተጫዋች ሲሆን ሌሎች ዘጠኝ ጎሎች የተቆጠሩት በሳጥን ውስጥ ተመትተው ነው።

– አማኑኤል ገብረሚካኤል በዚህ ሳምንት በጭንቅላቱ ገጭቶ ጎል ያስቆጠረ ብቸኛ ተጫዋች ነው ።

– እንደባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሁሉ 10 ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት ጎል አስቆጥረዋል። አማኑኤል ገብረሚካኤል በሁለት ጎል ቀዳሚ ሲሆን ቀሪዎቹ ጎሎች በዘጠኝ የተለያዩ ተጫዋቾች ተቆጥሯል።

– ሱራፌል ዐወል፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ፍስሐ ቶማስ፣ ፀጋዬ ባልቻ እና ወንድማገኝ ኃይሉ የውድድር ዘመኑ የመጀመርያ ጎላቸውን ያስቆጠሩት በዚህ ሳምንት ጨዋታዎች ነው።

– ስምንት ተጫዋቾች በጎል ማመቻቸት ተሳትፎ አድርገዋል።

– ጎል በማስቆጠርም በማመቻቸትም የተሳተፉ ተጫዋቾች ሁለት ሲሆኑ ጌታነህ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል አንድ ጎል እና አንድ አሲስት አስመዝግቧል።

– ፋሲል ከነማ ከአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ጎል አስተናግዷል። ሚኬል ሳማኬ በ5ኛው ሳምንት በምንይሉ ወንድሙ ጎል ከተቆጠረበት በኋላ በወንድማገኝ ኃይሉ ጎሉ እስኪደፈር ድረስ በአጠቃላይ 479 ደቂቃዎች ጎል ሳይቆጠርበት ዘልቋል። ይህም በውድድር ዘመኑ ከፍተኛው ነው።

– ሰበታ ከተማ ለሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል።

– አቡበከር ናስር ከስድስት ተከታታይ ጨዋታ በኋላ ጎል እና መረብ ሳያገናኝ ወጥቷል።

– አማኑኤል ገብረሚካኤል በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ የመጀመርያ ጎሉን አስቆጥሯል። አማኑኤል በፕሪምየር ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ ጎል ያስቆጠረው በተሰረዘው የውድድር ዘመን ጥር 2 ቀን 2012 መቐለ ከሜዳው ውጪ ወልቂጤን 1-0 በረከቱበት ጨዋታ ነበር።

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በአስራ ሁለተኛው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች 30 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲመዘዙ ሁለት የቀይ ካርዶች ተመዘዋል።

– በረከት ወልዴ እና ጀማል ጣሰው (ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ) የቀይ ካርድ የተመለከቱ ተጫዋቾች ናቸው።

– ጅማ አባ ጅፋር በአምስት ቢጫ ካርዶች ከፍተኛውን የካርድ ቁጥር አስመዝግቧል ።

– ሱሌይማን ሀሚድ እና አምሳሉ ጥላሁን የውድድር ዓመቱን አምስተኛ የማስጠንቀቂያ ካርድ በመመልከት ቀጣዩ ጨዋታ የሚያልፋቸው ተጫዋቾች ሆነዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ