አቡበከር ናስር የዓመቱን ሦስተኛ ሐት ትሪክ በሰራበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በ13ኛው ሳምንት መክፈቻ አዳማ ከተማን 4-1 አሸንፏል ።
ራሳቸውን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን የተናገሩት አሰልጣኝ አስቻለው በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈው ስብስብ ሦስት ለውጦችን በማድረግ በቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሄር ፣ ዳንኤል ተሾመ እና ጀሚል ያዕቆብ ምትክ ሙጃይድ መሐመድ ፣ ታሪክ ጌትነት እና በላይ ዓባይነህን አሰልፈዋል።
አሰልጣኝ ካሣዬ በበኩላቸው ከሆሳዕና አቻ ከተለያየው ስብስብ ሁለት ለውጥ በማድረግ ምንተስኖት ከበደ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን ወደ አሰላለፍ አምጥተው ወንድሜነህ ደረጄ እና ዊልያም ሰለሞንን አሳርፈዋል።
የመጀመርያው አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡና የጨዋታ የበላይነት የታየበት ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ አዳማ የጎል ክልል በመደረስ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። ሆኖም ከሌላው ጊዜ በተለየ አጨራረሳቸው እጅግ ደካማ የነበሩ በመሆኑ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በ9ኛው ደቂቃ ሚኪያስ እና አቡበከር ተቀባብለው ወደ ሳጥን በመግባት አቡበከር በግራ እግሩ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረበት ፣ በ15ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ በቅብብል ወደ ውስጥ በመግባት ሚኪያስ ሞክሮ ታሪክ ጌትነት በቀላሉ የተቆጣጠረው ፣ በ31ኛው ደቂቃ አሥራት ቱንጆ ከመስመር መሬት ለመሬት ያሻገረውን ደስታ ጊቻሞ ከአቡበከር ቀድሞ ያወጣው ፣ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ፍቅረየሱስ የመታው በረኛ ሲመልሰው አሥራት በድጋሚ መክሮ አጠገቡ የነበረው ታሪክ የመለሰበት ቡና ካልተጠቀመባቸው ዕድሎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በአጋማሹ አመዛኙን ጊዜ በራሳቸው የሜዳ ክፍል ተገድበው የተጫወቱት አዳማዎች በጥቂት አጋጣሚዎች ወደተጋጣሚ የጎል ክልል የደረሱ ቢሆንም በፈጠሩት አንድ ዕድል ጎል አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። በ39ኛው ደቂቃ በላይ ዓባይነህ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ቢሆንም በረዳት ዳኛው ዕይታ ያልገባው አብዲሳ ጀማል በአግባቡ ተጠቅሞ የዓመቱን ስድስተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል።
እንደመጀመርያው ሁሉ የቡናማዎቹ የበላይነት በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ቡናዎች በጎል ፊት የነበራቸውን ድክመት በሚገባ አሻሽለው በመግባት አራት ጎሎች አስቆጥረዋል። ገና ከጅምሩ ዕድል መፍጠራቸውን የቀጠሉት ቡናዎች በ58ኛው ደቂቃ አቻ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። ድንቅ የሁለተኛ አጋማሽ ያሳለፈው ታፈሰ ሰለሞን ያሻማውን ኳስ አቡበከር ናስር በግንባር ገጭቶ ወደ ጎልነት በመቀየር ነበር ቡናን አቻ ያደረገው።
ከጎሉ አንድ ደቂቃ ሳይሞላ በአቤል አማካኝነት ጠንካራ ሙከራ አድርገው ታሪክ ጌትነት እንደምንም ባወጣው እንዲሁም በድጋሚ አቤል ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ በወጣበት ሙከራ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የጣሩት ቡናዎች በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች የጎሉ መንገድ ቀላል ሆኖላቸዋል። በዚህ ዓመት የሚያቆመው ያልተገኘው አቡበከር ናስር በእዮብ ማቲያስ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አቡበከር ታሪክን አቅጣጫ አስቶ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ወደ መሪነት ሲያሸጋግር በ88ኛው ደቂቃ ደግሞ ከእንዳለ ደባልቄ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ የመታው ኳስ ሲመለስ በድጋሚ አግኝቶ በማስቆጠር የውድድር ዘመኑን ሦስተኛ ሐት ትሪክ መሥራት ችሏል።
ከጎሉ በኋላ ደስታ ጊቻሞ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣ ሲሆን እስከዛሬው ጨዋታ ድረስ እያንዳንዱን ደቂቃ ተጣማሪው ሆኖ የተጫወተው ትዕግስቱ አበራም በደረሰበት ጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል። በጭማሪው ደቂቃ ደግሞ ከማዕዘን ምት ተቀይሮ የገባው ኢያሱ ታምሩ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ታፈሰ ሰለሞን የዕለቱን የማሳረጊያ ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ