የአሠልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-4 ኢትዮጵያ ቡና

አምስት ግቦች ከተስተናገዱበት የ13ኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው?

ጥሩ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ላይም የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለን ነበር። ነገርን ዕድሎቹን ወደ ጎልነት መቀየር አልቻልንም። የመጀመሪያ አላማችንም ግን ይህ ነበር። እነሱ ቁጥራቸውን አብዝተው ይከላከሉ ስለነበር የግብ ዕድሎችን መፍጠር የሚል ተቀዳሚ አላማ ነበረን። ከእረፍት በኋላም ዕድሎችን የመፍጠር ስራ ላይ እንድንቀጥል ተነጋግረን ገብተናል። በዚህም ጥሩ ሆነን ጎሎችን አስቆጥረናል።

ቡድኑ በአንደኛ ዙር ውድድሩ ስለነበረበት ድክመት?

የመጫወቻ ቦታዎች ሲጠቡ አስተውሎ የመጫወት ችግር ነበር። በእንደዚግ አይነት ቦታ ግንኙነቶች ፈጣን መሆን አለባቸው። ምክንያቱም በዛ ጠባብ ቦታ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ስለሚኖሩ ኳሶች ይበላሻሉ። ስለዚህ ይህንን ነገር ማረም አለብን ብዬ አስባለሁ።

ስለ አቡበከር ናስር ብቃት?

የቡድኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋች አቡበከር ነው ማለት ይቻላል። ግን ደግሞ እሱንም የቡድኑ እንቅስቃሴ ጠቅሞታል። እንደ ቡድን በምናጠቃበት ጊዜ በቁጥር ብዙ ሆነን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ስለምንደርስ ተጫዋቾች ማንን መያዝ እንዳለባቸው ይቸገራሉ። ይህ ደግሞ አቡበከርን አግዞታል። ግን ደግሞ ብዙ ትኩረት እየተደረገበት ይህንን ሁሉ ግቦች ማስቆጠር መቻሉ ደግሞ የእርሱን ብቃት ያሳያል።

ስለ ዋንጫ ፉክክሩ?

ሲጀመር ቡና ሁል ጊዜ ለሻምፒዮንነት የሚጫወት ቡድን ነው። በእርግጥ ክለቡ ከእኔ ጋር ያለው ስምምነት ይታወቃል። ለቡድኑ አዲስ አሠልጣኝ እንደመሆኔ እና የምንጫወትበት መንገድ ትንሽ ለየት ያለ ስለሆነ ቡድኑን በደረጃ ደረጃ እያሳደጉ ለመምጣት ስምምነት አለን። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ቡና ሁል ጊዜም ለሻምፒዮናነት የሚታሰብ ቡድን ነው።

አስቻለው ኃይለሚካኤል – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

ብዙም የተለየ ነገር የለውም። በጨዋታው የነበረንን ደካማ ጎን ቡናዎች አይተው ከእረፍት መልስ ግቦችን አስቆጥረው አሸንፈውን ወተዋል። በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።

ቡድኑ ስለተከተለው አጨዋወት?

ቡና ኳስ መስርቶ መጫወት የሚፈልግ ቡድን እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም እኛ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር አስበን የገባነው። ነገርግን ያሰብነው አልተሳካልንም። በአጠቃላይ እነሱ ብልጫ ወስደው አሸንፈውናል።

ስለ አንደኛ ዙር የቡድኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ?

ከነበረን የዝግጅት ሁኔታ አኳያ የሚታሰቡ ነገሮች አሉ። ኳሊቲም ቡድንህ ውስጥ ሊኖር ይገባል። በተጨማሪም ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሩ መልካም ነው። እንደሚታወቀው ሌሎቹ ቡድኖች ብዙ ገንዘብ አውጥተው ነው የተሰሩት። የእኛ ግን እንደምታቁት ነው። ባለን አቅም ነበር ስንዘጋጅ የቆየነው። ይሄ ነገርም እንደሚደርስብን ቀድመን አስበን ነበር። ነገርግን እንስራ በሚል ሀሳብ ነበር የገባንበት። አሁን የክለቡ የበላይ አመራሮች ዘግይተው ነው ለክለቡ የደረሱት። ቀድመው ቢሆን ኖሮ ጥሩ ነበር። ብዙ ሮሮ አሰምተን ነው የተሰማነው። እኔም አዳማ በሁለተኛ ዙሩ ጥሩ ውጤት እንዲገጥመው እመኛለሁ።

ስለ ምክትል አሠልጣኞቹ ቀጣይ ቆይታ?

ከምክትል አሠልጣኞቼ ጋር በመከባበር እየተስማማን እስካሁን ስንሰራ ነበር። በተረፈ ግን ግንባር ወይንም እድል ያስፈልጋል። ስለዚህ የእኔ መቆየት አስፈላጊ አይሆንም። ሁለቱም ጓደኞቼ ልምድ ያላቸው ናቸው። መስራትም ይችላሉ። ማጠናከሪያም ከተደረገላቸው ጥሩ ውጤት ማምጣት ይችላሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ