ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ ከአቃቂ ላይ ሦስት ነጥብ አግኝቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የሁለተኛ ቀን የአስራ ሁለተኛ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታ በመከላከያ እና አቃቂ ቃሊቲ መካከል ተከናውኖ መከላከያ ተቸግሮም ቢሆን 2ለ0 ረትቷል፡፡

ረፋድ 4፡00 ሲል በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በጀመረው ጨዋታ መከላከያዎች እስከ አሁን ከመጡበት ውጤታማ ጉዞ አንፃር በቀላሉ በአቃቂ ላይ ብልጫን በመውሰድ ድል ያደርጋል የሚሉ ግምቶች የነበሩ ቢሆንም አቃቂ ቃሊቲዎች ግን በመከላከል ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ የጨዋታ አቀራረብን ይዘው በመቅረብ በተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ብልጫን ሲወስዱ ተመልክተናል፡፡ ለዚህም ማሳያነት ቤዛዊት ንጉሤ ከተሰለፈችበት የቀኝ መስመር ቦታ በተደጋጋሚ ወደ የመከላከያ ተከላካዮች ሰብራ ለመግባት በተደጋጋሚ የሞከረችበት እና ሁነኛ ሊያግዛት የሚችል የቡድን አጋር ባለመኖሩ ሲባክኑ የታየበት አቃቂዎች ስለ መሻላቸው በሚገባ ገላጭ ነበር፡፡ቀለሟ ሙሉጌታ በሁለት አጋጣሚዎች አቃቂዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ከግራ የመከላከያ የግብ ክልል አቅጣጫ በቀጥታ መትታ ታሪኳ በርገና በቀላሉ የያዘችባትም ሌላኛው የአሰልጣኝ ብዙዓየው ዋዳው ክለብ ሌላ ያገኙት አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

ካለፉት ጨዋታዎቻቸው በዚህኛው አጋማሽ ተዳክመው የታዩት መከላከያዎች ከተሻጋሪ ኳስ እና ከማዕዘን በተሻሙ ኳሶች ወደ አቃቂ የግብ ክልል ለመጠጋት ሞክረዋል፡፡ በተለይ ከግራ መስመር መሳይ ተመስገን በቀጥታ የምትመታቸው አደገኛ ኳሶች ከፊት ተሰልፈው የነበሩ አጥቂዎች የአጠቃቀም ደካማነት በጉልህ ይታይባቸው ስለነበረ ያገኟቸውን ዕድሎች በአግባቡ ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡ ቀዳሚው አርባ አምስት ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃ ብቻ ሲቀረው በግራ በኩል ከማዕዘን ጠርዝ ወደ ፊት በተጠጋ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት አስናቀች ትቤሶ አክርራ መታ ታሪኳ በርገና እንደምንም መልሳው በድጋሚ የአቃቂ አጥቂዎች በቀላሉ አስቆጠሩ ሲባል መከላከያዎች ተረባርበው ኳሷን አውጥተውታል፡፡

ከእረፍት መልስ አቃቂ ቃሊቲዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴያቸው ሳይወርዱ በድጋሚ የቀረቡ ቢሆንም የተጫዋች ለውጥ ያደረጉት መከላከያዎች ግን ባደረጉት ፈጣን የኮሪደር አጨዋወት ሁለት ጎሎችን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ 63ኛው ደቂቃ ላይ አቃቂዎች መጠቀም የነበረባቸውን መልካም አጋጣሚ ካመከኑ ከደቂቃዎች በኃላ በመልሶ ማጥቃት ፈጣን ሽግግር ወደ አቃቂ ግብ ክልል ተቀይራ በገባችው አይዳ ዑስማን አማካኝነት ወደ ፊት የደረሱ ሲሆን በመጨረሻም ለሴናፍ ሰጥታት አጥቂዋ ነፃ አቋቋም ለነበረችው ሥራ ይርዳው አመቻችታ አቀብላት ተጫዋቿም በቀላሉ ወደ ጎልነት ለውጣው መከላከያን መሪ አድርጋለች፡፡

ጎል የተቆጠረባቸው የማይመስሉት አቃቂዎች በተደጋጋሚ አቻ መሆን የሚችሉበትን ዕድል ቢያገኙም ኳስ እና መረብን የሚያገናኝ አጥቂ ያለ መኖሩ ቡድኑን ዋጋ አስከፍሏል፡፡ 81ኛው ደቂቃ ላይም የመስመር ተከላካይዋ ምህረት ተሰማ በረጅሙ ያሻገረችላትን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ በግንባር በመግጨት አስቆጥራ መከላከያን 2 ለ 0 እንዲያሸንፍ አስችላለች፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የአቃቂዋን ተጫዋች ቤዛዊት ንጉሴን የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ