“…እርሷ ብዙ ነገሬን ለውጣዋለች” – ታፈሰ ሰለሞን

ዘንድሮ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጭ በብዙ መልኩ ተለውጦ የመጣው ታፈሰ ሰለሞን የሚናገረው ነገር አለ…
የቀድሞ የኒያላ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ ድንቅ አማካይ ቡናማዎቹን ከተቀላቀለበት ጊዜ አንስቶ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። በተለይ በዘንድሮ ዓመት ብዙ ጊዜ ከሜዳ ውጭ የሚነሳበትን ጉዳዮች አስተካክሎ በመምጣት ምርጥ አማካይ መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል። ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን 4-1 በረታበት ጨዋታ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ጎል ያስቆጠረ ሲሆን ለጎል የሚሆኑ ኳሶችንም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ታፈሰ ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

” ተለውጬ ተረጋግቼ ጥሩ ጊዜ እንዳሳልፍ የፍቅር ጓደኛዬ አስተዋፆኦ ከፍተኛ ነው። እርሷ ብዙ ነገሬን ለውጣዋለች። ከዚህ በፊት ከሜዳ ውጭ የሚነሱብኝ ተለያዩ ድክመቶች ነበሩ። አሁን ግን በሁሉም ነገር እርሷ ረድታኛለች። ዛሬ እንኳን ጎል ሳታገባ እንዳትወጣ ብላ ስታነሳሳኝ ነበር። በአጠቃላይ በፊት መዝናናትን አበዛ ነበር። አሁን ሁሉን ነገር እረስቸዋለው። ከሜዳ ውጭ ያለውን ህይወቴ እርሷ በመቀየሯ ትኩረቴ እግርኳሱ ላይ ብቻ በማድረግ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፍኩ እገኛለሁ።

” አቡበከር ሐት ትሪክ ሰርቶ ተንበርክኬ ጫማውን በመጥረግ አክብሮቴን የገለፀኩለት ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ በጣም ስለምፈልግ ነው። ብዙ ጊዜ አይታችሁ እንደሆነ ኳሶቼ እርሱን ይፈልጋሉ። ገና የሊጉ ውድድር ሳይጀምር ለጌታነህ ከበደ ‘አቡበከር የአንተን ሪከርድ ይሰብራል ብዬ ነግሬው ነበር።’ ምክንያቱም የአቡበከር እንቅስቃሴ ያስታውቅ ነበር። እርሱ ጎል እንዲያገባ ካለኝ መጓጓት የተነሳ ነው ዛሬ ጎል ሲያገባ ያንን ያደረኩት። ባለፈው ጎል ሳያገባ ሲወጣ ራሱ በጣም ነበር የተናደደኩት።

” ቡድናችን ከባለፈው ዓመት የተሻለ ሆኖ ነው በዚህ ዓመት የቀረበው። በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ያለ ቡድን ነው። በግሌ ዓምና በጉዳት ብዙ ጨዋታ አልተጫወትኩም ነበር። ዘንድሮ ግን ራሴን በህይወቴም ተለውጬ ልምምድ ላይ ጠንክሬ በመስራት የተሻለ ነገር እየሰራሁ ነው።

” ከፍቅረኛዬ ጋር የጋብቻ ህይወት ለመመስረት አስበናል። አንዳንድ የምንዘጋጅባቸው ነገሮች እንዳለቁ በቅርቡ ጋብቻችን እውን ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ