ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ሰበታ ከተማ

የሳምንቱን አራተኛ ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

ፋሲል ከነማ ካሳለፍነው ሳምንት በተለየ ተከታዮቹ ድል ቀንቷቸው በመሀላቸው ያለውን ልዩነት ዝቅ በማድራጋቸው ክፍተቱን ወደነበረበት ወደ ሰባት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል። በተከታታይ ሁለት ድሎቹ ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ ያለው ሰበታም በመሀለኛው የሰንጠረዡ ክፍል መደላለደል ለመጀመር የሊጉን መሪ ጉዞ መግታት ይኖርባታል።

ተከታታይ ስድስተኛ ድላቸው ላይ የደረሱት ፋሲል ከነማዎች አካሄዳቸው በውጤት የታጀበ ከመሆኑ ባለፈ ለዋንጫ እንደሚጫወት ቡድን በተጋጣሚዎቻቸው ላይች ሥነ ልቦና ብልጫን ሲወስዱም ይታያል። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ሀዋሳን በገጠሙበት ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ከፍ ያለ ብልጫን ወስደው በቶሎ ግብ ማስቆጠር እና መምራት መቻላቸው ነው። በዚህ ረገድ በተቃራኒው በወልቂጤ ከተማ ብልጫ ተወስዶበት የጀመረው ሰበታ የጨዋታ ሀሳቡን ሰብስቦ ከፍ ባለ ትኩረት ካልጀመረ ለሊጉ መሪዎች በሩን ክፍት ሊያደርግ ይችላል።

መሀል ሜዳ ላይ ሰፋ ያለ የተጫዋቾች ምርጫ ያለው ፋሲል በሱራፌል ዳኛቸው ተሻሻሎ መቅረብ ጭምር የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አማካዮቹን ቀጥር አብዝቶ ጨዋታውን ይጀመራል የሚል ግምት አለ። ይህም የሰበታን የኳስ ቁጥጥር በመቋረጥ በቶሎ ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር ለቡድኑ ጥሩ አማራጭ ሊሆነው ይችላል። በቅርብ ጨዋታዎች ሙጂብ ቃሲም ላይ የተጣለ ይመስል የነበረው ግብ የማስቆጠር ኃላፊነት በሌሎች ተጨዋቾችም መታገዝ መጀመሩ ለአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን ሌላው በበጎ ጎኑ የሚነሳለት ነጥብ ሆኗል።

ሰበታ ከተማ ከሁለቱ ተከታታይ ድሎቹ ውጪ ለሦስት ጨዋታዎች ጎል አለማስተናገዱ ቀልብን የሚስብ ነው። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱም የመሳይ ጻውሎስ እና አንተነህ ተስፋዬ የመሀል ተከላካይ ጥምረት እንደሚፈልጉት የሆነ ይመስላል። ነገ ደግሞ በሊጉ ጠንካራ የማጥቃት አቅም ካላቸው ቡድኖች አንዱ የሆነው ፋሲልን ማግኘታቸው ይህንን ጠንካራ ጎናቸውን ብቃት ለመመዘን ሌላ ዕድል ይሰጣል። ያም ቢሆን አሰልጣኝ አብርሀም የመሀል ክፍላቸውን ሲያዋቅሩ ለተከላካይ መስመራቸው ከሚሰጠው ሽፋን በላይ ኳስን መስርቶ ለመውጣት ለሚኖረው አበርክቶ ቅድሚያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ በሆነው በዚሁ አማካይ ክፍሉ ላይ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾቹን ግልጋሎት ማግኘት ከቻለ የተጋጣሚውን ፈጣን እንቅስቃሴ በኳስ ቁጥጥር የማለዘብ እና ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ያስተናገደ የኋላ ክፍሉን ክፍተት ዳግም ለማሳየት በቅብብሎች መነሻነት ለአጥቂዎቹ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሞክር ይታሰባል። እዚህ ላይ ግን ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከመረብ ያገናኛቸው ኳሶች ከቆሙ ኳሶች መነሻነት መገኘታቸው ሲታሰብ ከክፍት ጨዋታዎች የሚፈጠሩ ዕድሎችን ወደ ግብ መቀየሩ ላይ ተሻሽሎ መቅረብ እንደሚኖርበት መገንዘብ ይቻላል።

ፋሲል ከነማ የግራ መስመር ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁንን በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ያጣል። ከዚያ ውጪ ቴዎድሮስ ጌትነት ጉዳት ላይ ሲገኝ ከባድ ጉዳት ላይ የሰነበተው ሰዒድ ሁሴን ልምምድ መጀመሩን ሰምተናል። ሰበታ ከተማ በበከሉ ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ጌቱ ኃይለማርያም እና ቢያድግልኝ ኤልያስ እንደሙመለሱለት ሲጠበቅ ፉዓድ ፈረጃ ግን በወልቂጤው ጨዋታ ከገጠመው ጉዳት አላገገመም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በተሰረዘው የውድድር ዓመት በአስገራሚ መልኩ ስድስት ጎሎችን ባስተናገደው ጨዋታ 3-3 ከመለያየታቸው ውጪ ተገናኝተው የማያውቁት ሁለቱ ክለቦች ነገ የመጀመሪያ ጨዋታቸቅን የሚያደርጉ ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኬ

እንየው ካሣሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ሀብታሙ ተከስተ

በረከት ደስታ – ሱራፌል ጌታቸው – በዛብህ መለዮ – ሽመክት ጉግሳ

ሙጂብ ቃሲም

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት ዓሎ

ዓለማየሁ ሙለታ – መሳይ ጻውሎስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

መስዑድ መሀመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ

ኢብራሂም ከድር – ፍፁም ገብረማርያም – ቡልቻ ሹራ


© ሶከር ኢትዮጵያ