በቅርቡ አዲስ አሠልጣኝ የሾሙት ጅማ አባጅፋሮች አንድ ተጫዋች ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ቅድመ ስምምነት ፈፅመዋል።
የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ክለብ የሆነው ጅማ አባጅፋር በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ባሳየው ደካማ ብቃት የወራጅ ቀጠናው ቦታ ላይ ይገኛል። የክለቡ አመራሮችም ከአሠልጣኝ ጻውሎስ ጋር ከተለያዩ በኋላ በሊጉ ልምድ ያላቸውን አሠልጣኝ ፀጋዬን በመሾም ካሉበት ወራጅ ቀጠና ለመውጣት እየጣሩ ይገኛሉ። አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምም ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ተጠናክሮ እንዲቀርብ በዛሬው ዕለት አንድ ተጫዋች ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል መስማማታቸው ተረጋግጧል።
ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ተጫዋች አማኑኤል ተሾመ ነው። የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ፣ ወላይታ ዲቻ፣ መከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች የነበረው የተከላካይ አማካዩ አማኑኤል ያለፉትን ስድስት ወራት ዳግም ወደ ወላይታ በማምራት መጫወቱ ይታወሳል። ተጫዋቹም በሊጉ በርካታ ግቦችን እያስተናገደ ለሚገኘው የቡድኑ የተከላካይ መስመር ሽፋን በመስጠት ቡድኑን ያጠናክራል ተብሎ ይገመታል።
© ሶከር ኢትዮጵያ