ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአስራ ሁለተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ተደርጎ ያለ ጎል 0ለ0 ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው አስቀድሞ በአንደኛው ዙር የልሳን የሴቶች ስፖርት ምርጥ ተጫዋች የተባለችው ማዕድን ሳህሉ ሽልማቷን ተቀብላለች፡፡

ተመሳሳይ የአጨዋወት ይዘትን ባየንበት እና ደካማ የአጥቂ ክፍልን በተመለከትንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋዎች በተለይ ከቆመ ኳስ እና ከርቀት እድል ፈጥረዋል። 8ኛው ደቂቃ ፀጋነሽ ወራና ከግራ አቅጣጫ የተገኘን ቅጣት ምት አክርራ መታ የኤሌክትሪኳ ግብ ጠባቂ ትዕግስት አበራ ያወጣቻት ኳስ የጨዋታው ቀዳሚ ሙከራም ነበረች፡፡

ቀስ በቀስ በመስመር አጨዋወት ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ኤሌክትሪኮች በግራ መስመር በተሰለፈችው እፀገነት ብዙነህ አማካኝነት ለማጥቃት ሲታትሩ ተስተውሏል፡፡ ከመስመር አጨዋወታቸው በዘለለ ቤዛዊት ተስፋዬ እና ፅዮን ፈየራ መሐል ሜዳው ላይ በፈጠሩት አስደናቂ ቅንጅት ወደ ፊት በመጣል ተፅዕኖ ለመፍጠር ቢሞክሩም የመጨረሻው የኳሱ ማረፊያ ስኬታማ ባለመሆኑ ያሰቡትን እቅድ ለመተግበር አላስቻላቸውም፡፡ በፀጋነሽ ወራና ላይ ማጥቃቱ ጥገኛ ይመስል የነበረው ድሬዳዋ ከተማ አጥቂዋ 40ኛ ደቂቃ አክርራ መታ ብረት የመለሰባት አስቆጪ ሙከራ ሌላኛው አደገኛ አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም በተሻሻለ አቀራረብ ወደ ሜዳ የተመለሰ ሲሆን በእንቅስቃሴ ድሬዳዋዎች ባይታሙም በማጥቃቱ ላይ ከመጀመሪያው አርባ አምስት ደክመው ታይተዋል፡፡ ሣራ ነብሶ እና እፀገነት ብዙነህ ከርቀት በሞከሩት ሙከራ ወደ ጎል ለመጠጋት የቻሉት ኤሌክትሪኮች በተደጋጋሚ ከመስመር በተጨማሪ ከመሐል ሜዳ በሚነሱና ወደ ታታሪዋ አጥቂ ዮርዳኖስ ምዑዝ በሚሻገሩ ኳሶች ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል ሲደርሱ ተመልክተናል፡፡ 53ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የድሬዳዋ ግብ ክልል ወደ ማዕዘን ምት አቅጣጫ ባለ ቦታ የተሰጠውኝ የቅጣት ምት ምት መሰሉ አበራ ወደ ጎል ስታሻማ ነፃ አቋቋም ላይ ቆማ የነበረችው ሣራ ነብሶ በግንባሯ ገጭታ አስቆጠረች ሲባል ወደ ውጪ ኳሷ አቅጣጫዋን ለውጣ ወደ ውጪ በግቡ ብረት ስር ታካ ወጥታለች። 60ኛው ደቂቃ አጥቂዋ ሳራ ነብሶ በሳጥን ውስጥ በጭርፍራፊ መንገድ የመጣችን ኳስ ከግራ በኩል እንደምንም ተጫዋቾችን አልፋ የሰጠችውን ኳስ በጨዋታ ጥሩ ጊዜ የነበራት ፅዮን ፈየራ አግኝታ በቀጥታ መታው በተከላካዩች ተደርባ ኳሷ ስትመለስ በድጋሚ ዮርዳኖስ ምዑዝ በቦሊ ስተመታው ሂሩት ደሴ ይዛባቸዋለች፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች ቆይታ መልስ በቅብብል የድሬዳዋ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅማ ዮርዳኖስ ምዑዝ አሁንም በድጋሚ ለኤሌክትሪክ አስቆጠረች ተብሎ ሲጠበቅ ሳይታሰብ ወደ ውጪ ሰዳዋለች፡፡ ኤሌክትሪኮች አሁንም በዮርዳኖስ ምዑዝ አማካኝነት ተደጋጋሚ ጥረቶች ማድረግ ቢችሉም ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ግን አልተቻላቸውም፡፡

በእንቅስቃሴ ጥሩ መስለው ቢታዩም በሙከራ ረገድ በተጋጣሚያቸው ለመበለጥ የተገደዱት የአሰልጣኝ ብዙዓየው ጀምበሩው ድሬዳዋ ከተማዎች ለሚያገኟቸው ኳሶች ያደርጉት የነበረው ጥረት ደካማ በመሆኑ ብዙም የተሳኩ ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩ ተቀይራ የገባችው ቁምነገር ካሳ ድሬዳዋን አሸናፊ የምታደርግ አስገራሚ ኳስ ማግኘት ብትችልም የመታቻት ኳስ ጠንካራ ባለመሆኗ ትዕግስት አበራ ይዛባታለች፡፡ ጨዋታው ያለ ጎል ተፈፅሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ