የአሠልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-1 ሰበታ ከተማ

አንድ አቻ ከተጠናቀቀው የ9 ሰዓቱ ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞቹ ለሱፐር ስፖርት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው?

በአጠቃላይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልነበርንም። የኳስ ቁጥጥሩ በሰበታዎች በኩል ይሻል ነበር። እርግጥ እነሱ ማጥቃቱ ላይ ብዙም ባይመጡም ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረዋል። እረፍት ሰዓትም ይህንን ለማሻሻል ነበር የተነጋገርነው። በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ መተን ነበር። ነገርግን በመከላከል አደረጃጀታችን ያስተናገድነው ጎል ዋጋ አስከፍሎናል። በአጠቃላይ ግን እስካሁን ከተጫወትናቸው 12 የሊጉ ጨዋታዎች ለእኔ ጥሩ ያልሆነው ጨዋታ የዛሬው ነው። በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ጎል በመሔድ ያደረግነው እንቅስቃሴ ትንሽ ወረድ ያለ ነበር። በሁለተኛ ዙሩም እነዚሀን ሁሉ አሻሸለን በመቅረብ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ። እስካሁን ያገኘነው ነጥብ ግን በቂያችን ነው።

ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ?

ሰበታዎች የነበራቸው ነገር ጥሩ ነበር። ኳሱንም ተቆጣጥረውት ነበር። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸው ነገር መልካም ነበር። እኛም በሁለተኛው አጋማሽ ለመምጣት ሞክረናል። ግን ውጤታማ አልነበርንም። ጨዋታውን የምናሸንፍበት ዕድልንም አልተጠቀምንበትም። ምንም ይሁን ግን አንድ ነጥብም ውጤት ስለሆነ ጥሩ ነው።

ስለ ቡድኑ ደካማ ጎን?

ግብ ካስቆጠርን በኋላ ተጋጣሚዎች እንዲነሱ የምሰጠው ዕድል በሁለተኛ ዙር መስካከል አለበት። ምክንያቱም በጀመርነው ፍጥነት መቀጠል አለብን። ግብ ካገባን በኋላ ያለ መውረድ መጠነኛ ቢሆን ምንም አደለም። ግን እኛ በደንብ ነው የምንወርደው። ይሄም በብዙ ጨዋታዎች ታይተቷል። ስለዚህ ይህንን እናስተካክላለን።

አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

ጥሩ የጨዋታ ብልጫ ነበረን። የሜዳው ሦስተኛ ክፍል ላይም በመድረስ የተሻልን ነበርን። ነገርግን ግብ አካባቢ መረጋጋቶች ባለመኖራቸው ብቻ በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ማስቆጠር አልቻልንም። በተረፈ ግን ጨዋታውን በደንብ ተቆጣጠረን ነበር ማለት እችላለሁ። በሁለተኛው አጋማሽ የተመጣጠነ ጨዋታ ነበር። እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበርን ማለት አልችልም። ነገርግን ለማግባት በነበረ ፍላጎት ከኋላ የምንጀምርበትን ነገር ትንሽ ተበላሽቶብናል። ቢሆንም ግን መሪ ከሆነው ቡድን ጋር ነጥብ ተጋርቶ መወጣት እራሱ ለተጫዋቾቻችን የራስ መተማመን መንፈስ ጥሩ ነው።

የአቻነቱን ግብ ስላስቆጠረው ቡልቻ?

ቡልቻ ያለፉትን በርካታ ጨዋታዎች ጥሩ እየተንቀሳቀስ ግብ አላስቆጠረም ነበር። የአጥቂ መስመር ተጫዋች ደግሞ ግብ ማስቆጠር አለበት። ዛሬም ያስቆጠረው ጎል በሁለተኛው ዙር ያለው የራስ መተማመን እንዲዳብር ያደርጋል። ሁለተኛ ደግሞ በየትኛውም ጨዋታ ግብ ማስቆጠር እንደሚችል እንዲያምን ያደርገዋል።

በክፍት ጨዋታ ቡድኑ ግብ ስለማያስቆጥርበት ነገር?

በትክክል! በክፍት ጨዋታ ግብ ማስቆጠር የመቻል ክፍተት አለብን። በተደጋጋሚ ጊዜ እንደምለው በዝግጅት ጊዜ ብዙ ያልሰራናቸው ስራዎች አሉ። አንዱም ችግራችን በእንቅስቃሴ ግብ የማስቆጠር ነው። ምናልባት ሁለቱን ጨዋታ እዚሁ ጨርሰን ወደ ድሬዳዋ ከመሄዳችን በፊት ባለን ሰፊ ጊዜ የምናስተካክለው ይሆናል። በተጨማሪም ከጨዋታ ጨዋታ ይሄንን ነገር ለማስተካከል እንሞክራለን።

በሁለተኛው ዙር ቡድኑ ስላሰበው ነገር?

ሲጀመርም የነበረን ዓላማ ቡድኑን ተፎካካሪ አድርጎ በሊጉ ውስጥ እንዲቆይ ለማድረግ ነበር። በሁለተኛ ዙር ውድድርም ይሄንኑ ዓላማ ለማሳካት ጠንክረን እንሰራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ