ሪፖርት | ሰበታ ከተማ የፋሲል ከነማን ተከታታይ የአሸናፊነት ጉዞ ገታ

በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ያስመለከተው የፋሲል ከነማ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በ12ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ሀዋሳ ከተማን 2-1 ያሸነፉት ፋሲል ከነማዎች በጨዋታው ተጠቅመውት ከነበረው ቋሚ 11 አንድ ለውጥ ብቻ አድርገዋል። በዚህም በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት ቅጣት ያለበትን አምሳሉ ጥላሁንን በሳሙኤል ዮሐንስ በመለወጥ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ሰበታዎች በበኩላቸው ወልቂጤን 1-0 ካሸነፉበት ጨዋታ ፋዓድ ፈረጃ እና አለማየሁ ሙለታን በዳዊት እስቲፋኖስ እና ጌቱ ኃይለማርያም ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ታጅቦ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና ከአምስት ደቂቃ ሳይዘል ግብ አስተናግዷል። በ5ኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ ረጅም ኳስ በሀብታሙ ተከስተ አማካኝነት የላኩት ፋሲል ከነማዎች የሽመክት ጉግሳን ፍጥነት ተጠቅመው ያገኙትን የመስመር ላይ ኳስ ወደ ግብነት ቀይረዋል። ሽመክት በቀኝ መስመር ላይ ሮጦ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ለማሻማት በማስመሰል ወደ ግብ ልኮት ኳሱ የምንተስኖት መረብ ላይ አርፏል።

ሳያስቡት ገና በጊዜ መመራት የጀመሩት ሰበታዎች ለተቆጠረባቸው የመጀመሪያ ደቂቃ ጎል ምላሽ ለመስጠት መታተር ጀምረዋል። በዚህም ጨዋታው ሩብ ሰዓት ሳይሞላው በጌቱ እንዲሁም በ20ኛው ደቂቃ በዳዊት አማካኝነት ሙከራ ሰንዝረዋል።

ድንቅ የሜዳ ላይ ፉክክር እያስመለከተ የቀጠለው ጨዋታው በርከት ያሉ የኳስ ቅብብሎች ተስተውለውበታል። በተለይ ሰበታ ከተማዎች ከኳስ ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ በመጨመር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። ፋሲሎች በበኩላቸው በፈጣኖቹ የመስመር ላይ ተጫዋቾቻቸው በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በዚህ አጨዋወትም ሙጂብ ቃሲም በ31ኛው ደቂቃ ጥሩ ኳስ ወደ ግብ መትቶ መክኖበታል። ቡድኑ የመስመር ላይ ጥቃቶችን ከመሰንዘሩ በተጨማሪም የሙጂብ ቃሲምን ብቃት ለማግኘት ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ሰበታ የግብ ክልል ለመላክ ሞክሯል።

በአንፃራዊነት ኳስን በተሻለ ተቆጣጥረው ጨዋታውን እየከወኑ የሚገኙት ሰበታዎች ወደ ፋሲሎች የመጫወቻ ሜዳ ለመግባት ባይቸገሩም የመጨረሻው የማጥቂያ ሲሶ ላይ ሲደርሱ በሚወስኗቸው ስህተት የተሞላባቸው ውሳኔዎች አስፈሪነታቸው ቀንሶ ታይቷል። አጋማሹም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በፋሲል ከነማ 1-0 መሪነት ተገባዶ ተጫዋቾቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

መሪ እየሆኑ እረፍት የወጡት ፋሲሎች የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጠሪ በሆነው ሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ጥሩ ሙከራ አድርገው ነበር። የማጥቃት ሀይላቸውን ለማደስ የተጫዋች ለውጥ አድርገው አጋማሹን የጀመሩት ሰበታዎች በበኩላቸው በፈጠራ አቅማቸው ጥሩ በሆኑት የአማካይ መስመር ተጫዋቾቻቸው በመታገዝ አቻ ለመሆን መከራ መሰንዘር ይዘዋል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ጠንካራ ፉክክር ማስተናገድ ያልቻለው ይህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለግብነት የቀረበ ሙከራ ያስተናገደው በ70ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህ ደቂቃ ጥፋት ተሰርቶ የተገኘውን የቅጣት ምት የሰበታው አማካይ ዳዊት ከርቀት ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ሳማኪ አምክኖታል። የኳስ ቁጥጥር የበላይነታቸውን በግብ ለማጀብ ጥረታቸውን የቀጠሉት ሰበታዎች በ77ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን አገናኝተው አቻ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃም ሀብታሙ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው እስራኤል እሸቱ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የገኘውን የቅጣት ምት ዳዊት አሻምቶት ቡልቻ ሹራ በግንባሩ ግብ አስቆጥሯል።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ የነበራቸውን ፍጥነት፣ ፍላጎት እና ጉጉት በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቀንሶ ብልጫ የተወሰደባቸው ፋሲሎች ወደ ግብ የሚደርሱበት መንገድም ተገድቦ ታይቷል። በተቃራኒው በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር ያስቀጠሉት ሰበታዎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት የሞከሩበት መንገድ ፍሬ አፍርቶ ጨዋታውን አቻ አጠናቀዋል።

ውጤቱን ተከትሎ የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ በአንደኛ ዙር የሊጉ ጨዋታዎች የሰበሰባቸውን ነጥቦች 29 በማድረስ በአንደኝነቱ ቀጥሏል። ከመመራት ተነስተው አቻ የሆኑት ሰበታዎች ደግሞ ነጥባቸውን 14 በማድረስ የነበሩበት 8ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ