ሲዳማ ቡና ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን በማሰናበት አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን የሾሙት ሲዳማ ቡናዎች በሁለተኛው ዙር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተጠናክሮ ለመቅረብ ሥራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። በዚህም በዛሬው ዕለት ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀላቸው ተስማምተዋል።

ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው አንደኛው ተጫዋች መሐሪ መና ነው። ይህ የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የግራ መስመር ተከላካይ ከአምሰት ዓመታት የፈረሰኞቹ ባት ቆይታ በኋላ በክረምቱ ክለቡን መልቀቁ የሚታወስ ሲሆን በሲዳማ የሚስተዋለውን ተፈጥሯዊ የግራ መስመር ተከላካይ እጥረት ለመሸፈን ተቀላቅሏል ።

ሁለተኛው ሲዳማን የተቀላቀለው ተጫዋች ዮናስ ገረመው ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ጅማ አባ ጅፋር እና መቐለ 70 እንድርታ ተጫዋች የነበረው ዮናስ በትግራይ ክልል የሚጫወቱ ተጫዋቾች ለዚህ ዓመት ብቻ ወደ ሌሎች ክለቦች አምርተው እንዲጫወቱ በወጣው ልዩ የዝውውር ደንብ ተጠቅሞ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ለማምራት ተስማምቶ እንደነበር ይታወሳል። ነገርግን ተጫዋቹ እና ክለቡ የፈፀሙት ስምምነት ሳይፀድቅ በተከታታይ ሁለት ዓመታት የሊጉን ዋንጫ ያነሳው ተጫዋቹ የቀድሞ አሠልጣኙን የአማካይ መስመር ለማጠናከር ቡድኑን ተቀላቅሏል።

የመጨረሻው ሲዳማን ለማገልገል የተስማማው ተጫዋች ሽመልስ ተገኝ ነው። ለበርካታ ዓመታት በመከላከያ ግልጋሎት የሰጠው የቀድሞ የሙገር ሲሚንቶ የመስመር ተከላካይ ተጫዋች የነበረው ሽመልስ የቡድኑን የቀኝ መስመር ለማጠናከር ቡድኑ ወዳለበት ባህር ዳር ተጉዟል።

ተጫዋቾቹ ከነገ ጀምሮ በሚከፈተው የዝውውር መስኮት ውላቸውን በፌዴሬሽን ያስፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ