የ13ኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የተመለከትንበት ዳሰሳችን ይህንን ይመስላል።
በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ የሚገኙ ቡድኖችን እንደማገናኘቱ ጠንከር ያለ ፉክክር እንደሚደረግበት በሚጠበቀው በዚህ ጨዋታ ድል የሚቀናው ቡድን ሰበታን ተከትሎ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ የመጠጋት ዕድል ይኖረዋል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር የመጀመሪያ ድሉን እንዲያሳካ የፈቀደው ሲዳማ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈቱን ነበር ያስመዘገበው። በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ስር የመጀመሪያ ጨዋታውን ያከናወነው ቡድኑ በጥሩ የተነሳሽነት መንፈስ ላይ ሆኖ ቢታይም ከጉጉት የመነጨ የሚመስለው በግብ ፊት ያለው ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ትልቁ ደካማ ጎኑ ነበር። ኳስ እና መረብን ካገናኘ ሦስት ጨዋታዎች ያለፉት ሲዳማ በነገው ጨዋታም ከጠንካራ የተከላካይ ክፍል ካለው ቡድን ጋር እንደመገናኘቱ ይህንን ችግሩን በምን መልኩ ቀርፎ ይመጣል የሚለው ጉዳይ የሚያሳስበው ይሆናል። ቡድኑ በመስመር በኩል የማጥቃት አቅሙ መዳከሙ እና በቅብብሎች ወቅት በትዕግስት ሳጥን ውስጥ ከመድረሱ በፊት ከርቀት በሙደረጉ ሙከራዎች የሚያባክናቸው ኳሶችም እንደልብ ክፍተት በማይገኝበት የነገው ጨዋታ ሌላዎቹ ፈተናዎቹ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሲዳማ ቡና ጉዳት ላይ የሰነበተው አጥቂው ይገዙ ቦጋለ እና ላውረንስ ኤድዋርድን በጉዳት የሚያጣ ከመሆኑ ባሻገር ካለበት የአጨራረስ ችግር አንፃር ትልቅ እጦቱ የሚሆነው ደግሞ የማማዱ ሲዲቤ ለጨዋታው ብቁ አለመሆን ነው።
ተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ከተማን አላፈናፍን ብለው ነጥብ መጋራት የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ለሦስት ጨዋታዎች ከሽንፈት መራቅ ችለዋል። በነገው ጨዋታ ግን ከባለፈው አንፃር የተሻለ የማጥቃት ሀሳብን ይዘው እንደሚገቡ ይጠበቃል። በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲደርሱ በቁጥር የማነሳቸው ነገር በሲዳማ ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ ምክንያት ሊሆን ቢችልም ደጋግመው የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን መፍጠር ከቻሉ ግን ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ይኖራል። ያም ቢሆን በአመዛኙ በፀጋዬ ብርሀኑ እና ቢኒያም ፍቅሬ ፍጥነት ላይ የተመሰረተው የቡድኑ ፈጣን ሽግግር ለተጋጣሚው ተገማች እንዳያደርገውም ያሰጋል። በመሆኑም የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን በምን መንገድ የመከላከል አደረጃጀቱን ጥንካሬ ጠብቆ ኳስ ሲነጥቅ የመጨረሻ የግብ ዕድል ለመፍጠር በሚያስችል የቁጥር ብዛት እና ፍጥነት ተጋጣሚው ደጃፍ ይደርሳል የሚለው ጉዳይ ከነገው ጨዋታ ይጠበቃል።
ድቻዎች ወሳኙ አማካያቸው በረከት ወልዴን በቀይ ካርድ ቅጣት ሲያጡ በጉዳት የከረመው ስንታየሁ መንግሥቱም ለተሻለ ህክምና ወደ አዲስ አበባ አምርቷል። ከዚህ ውጪ ባለፈው ጨዋታ በግል ጉዳይ ያልነበረው ኤልያስ አህመድ ወደ ቡድኑ መመለሱን ሰምተናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 12 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ በአምስት ጨዋታ አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና ስድስት ጊዜ አሸንፏል።
– በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 18 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 6፣ ሲዳማ ቡና 12 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-3-3)
ፍቅሩ ወዴሳ
ዮናታን ፍሰሀ – ፈቱዲን ጀማል – ጊት ጋትኮች – ግሩም አሰፋ
ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – ዮሴፍ ዮሃንስ
ተመስገን በጅሮንድ – ሀብታሙ ገዛኸኝ – ጫላ ተሺታ
ወላይታ ድቻ (4-3-3)
መክብብ ደገፉ
አናጋው ባደግ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – ያሬድ ዳዊት
መሳይ አገኘሁ – መሳይ ኒኮል – እንድሪስ ሰዒድ
ፀጋዬ ብርሀኑ – ቢኒያም ፍቅሬ – ቸርነት ጉግሳ
© ሶከር ኢትዮጵያ