ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አዲስ አበባ ከተማ የመጀመርያውን ዙር በመሪነት አጠናቋል

የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ስምንተኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ዛሬ መካሄድ ሲጀምር አዲስ አበባ የምድቡ መሪ ሆኖ ያጠናቀቀበትን ውጤት አስመዝግቧል። አባ ቡና ተጋጣሚውን በሰፊ የጎል ልዩነት ሲያሸንፍ ከፋ ቡና እና ጋሞ ጨንቻ አቻ ተለያይተዋል።

ረፋድ 4:00 የጀመረው የካፋ ቡና እና ጋሞ ጨንቻ ጨዋታ በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል። ገና በጨዋታው ጅማሬ ካፋዎች በተካልኝ መስፍን አማካኝነት ቀዳሚ ሆነዋል። በጨዋታው መጀመርያ ደቂቃ ላይ ጎል መቆጠሩን ተከትሎ ተጨማሪ ጎሎች በፍጥነት ይቆጠራሉ ተብሎ ቢገመትም የመጀመርያው አጋማሽ በዚሁ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል። 

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ጋሞ ጨንቻዎች ከእረፍት መልስ ወድያውኑ በ47ኛው ደቂቃ አቻ የሚሆኑበትን ጎል በኪሩቤል ፍቅረ ማርቆስ አማካኝነት ሲያስቆጥሩ በ67ኛው ደቂቃ በአሸናፊ ተገኝ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው እስከ 85ኛው ደቂቃ መምራት ችለው የነበሩ ቢሆንም በመጨረሻ ደቂቃ ኤልሻዳይ ሕገመንግስት ለከፋ ቡና አቻ የምታደርግ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሁለት አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ቀትር ስምንት ሰዓት በተካሄደው የነቀምቴ ከተማ እና የጅማ አባ ቡና ጨዋታ አባቡናዎች ከጨዋታ ብልጫ ጋር አራት ለምንም አሸንፈዋል። በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ ሆነው ለመቅረብ ነቀምቴዎች ጥረት ቢያደርጉም በጎል ያልታጀበ እና አጨዋወታቸው ብዙ ያልዘለቀ በመሆኑ የኃላ የኃላ ወደ ጨዋታው በመግባት ወደ ነቀምቴ የግብ ክልል በመድረስ የጎል ዕድሎችን መፍጠር የጀመሩት አባ ቡናዎች ድል አድርገዋል። 25ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ፊት ለፊት የተሰጠውን ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ፋይሰን ሙዘሚል በቀጥታ ወደ ጎልነት በመቀየር አባ ቡናዎችን መሪ አድርጓል።

ከመጀመርያው አጋማሽ ወርደው የታዩት ነቀምቴዎች ተጨማሪ ጎሎች እንዲቆጠርባቸው ሆነው በ49 ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደፊት የሄዱት አባ ቡናዎች ከቀኝ መስመር ፋይሰን ሙዘሚል ያሻገረውን ጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ የነበረው ሱራፌል ፍቃዱ በግንባሩ ገጭቶ የአባቡና የጎል መጠንን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል። የአባቡናን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ መገደብ የተሳናቸው ነቀምቴዎች ጫና ፈጥረው ለማጥቃት ቢሞክሩም ያልተደራጀ እና ቶሎ የሚቆራረጥ በመሆኑ ጎሎች እንዳያስቆጥሩ ሲያደርጋቸው ተመልክተናል።

የጥንቃቄ አጨዋወት በመከተል ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ጎል ሲፈልጉ የቆዩት አባ ቡናዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ 86ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ኤልያስ እንድሪስ የአባቡና የግብ መጠን ማስፋት የቻሉበትን ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል። ለዚህች ጎል መቆጠር ጣጣውን የጨረሰ ኳስ በማቀበል ብርሀኑ ደስታ ሚና የጎላ ነበር። ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የቆየው ሱራፌል ፍቃዱ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአባ ቡና የበላይነት አራት ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

የዕለቱ የመጨረሻ እና ተጠባቂ ጨዋታ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ እና የኢኮሥኮ ጨዋታ በአዲስ አበባ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጥሩ ፉክክር ባስመለከተን በዚህ ጨዋታ አዲስ አበባዎች ከጨዋታው የሚፈልጉትን ውጤት ለማሳካት ተረጋግተው መጨዋወታቸው ውጤታማ መሆን አስችሏቸዋል። ጫና ፈጥረው በሚጫወቱበት አጋጣሚ ገና በጨዋታው ጅማሬ የኢኮሥኮ ተከላካዮች ኳስ በእጅ በመንካታቸው የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሮቤል ግርማ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከደቂቃዎች በኃላ አዲስ አበባዎች በአጥቂያቸው ዘርዓይ አማካኝነት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ቢያገኙም ሳይጠቀምበት መክኗል። አልፎ አልፎ ኢኮሥኮዎች የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ብዙ የተሳካ ባለመሆኑ ወደ ጎልነት ሳይቀየር ቢቀርም በአንድ አጋጣሚ የኃለሸት ሰለሞን እና ዳንኤል ከበደ ለጎሉ ሁለት ሜትር ርቀት ላይ የተገኘን ኳስ የኃላሸት መቶት ግብጠባቂው ሳምሶን አሰፋ እንደምንም በማዳን የተፋውን ኳስ ዳንኤል አግኝቶ አገባው ሲባል ተከላካዮቹ እንደምንም ተረባርበው ያዳኑት ኳስ የሚያስቆጭ ነበር።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት መንገድ ይዘው የመጡት አዲስ አበባዎች ድል የጨበጡባቸው ጎሎችን በዚህ አጋማሽ አግኝተዋል። በ50ኛው ደቂቃ አንበሉ ከድር ያሻገረለትን ዘርዓይ ገብረሥላሴ በግብጠባቂወ አናት ላይ ሰዶ አዲስ አበባን ቀዳሚ አድርጓል። በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ፈጠን የነበሩት አዲስ አበባዎች በ57ኛው ደቂቃ ሌላ ተጨማሪ ጎል በዘርዐዓይ አማካኝነት አስቆጥረው መሪነታቸውን አስፍተዋል።

የአዲስ አበባ ግብጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ከግብ ክልሉ አራቅኩ ብሎ የመታውን ኳስ በማጠሩ ምክንያት በየነ ባንጃ ነፃ የጎል ዕድል አግኝቶ ወደ ግብ ክልሉ ቢመታውም ራሱ ሳምሶን ከሳጥን ውጭ የነበረ በመሆኑ በእጁ የማይነካውን ኳስ ተወርውሮ በግንባሩ በመመለስ አስገራሚ ብቃቱን አሳይቶናል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ኢኮሥኮዎች ጥረት ቢያደርግም ልምዱን እና የግብ ክልሉን በንቃት ይጠብቅ የነበረው ግብጠባቂው ሳምሶን ሲያመክንባቸው ውሏል። ኢኮሥኮዎች የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ መዳከማቸውን ተከትሎ ተጨማሪ ጎል አዲስ አበባዎች በተለይ በሁለት አጋጣሚ አቤል ብርሀኑ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ጨዋታውም በአዲስ አበባዎች 2–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታውም መጠናቀቅ በኃላ ምድቡን በአንደኝነት ማጠናቃቸውን ተከትሎ የቡድኑ አባላት በአንድነት በመሰባሰብ ደስታቸውን በአንድነት መንፈስ ሲገልፁ ተመልክተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ