ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት ቁጥራዊ መረጃዎች እና ዕውነታዎች

የ13ኛው ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና ቁጥሮችን እነሆ!

– በዚህ ሳምንት 16 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም 11 ጎሎች ካስተናገደው ያለፈው ሳምንት የተሻለ ቁጥር ነው።

– ስድስት ጎሎች በመጀመርያው አጋማሽ ሲቆጠሩ 10 ጎሎች በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተቆጥረዋል።

– ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛውን ቁጥር አስመዝግበዋል።

– ሰባት ጎሎች የተስተናገዱበት የወልቂጤ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ የሳምንቱ በርካታ ጎል የተቆጠረበት ሆኗል።

– አንድ የፍፁም ቅጣት ምት (አቡበከር) እና አንድ ቅጣት ምት (ጌታነህ) እንዲሁም መነሻቸው ከማዕዘን ምት የሆኑ ሁለት ጎሎች (ታፈሰ እና ጌታነህ) እና ከቅጣት ምት መነሻነት (ቡልቻ) ሲቆጠሩ ሌሎቹ 11 ጎሎች በክፍት ጨዋታ ተቆጥረዋል።

– በዚህ ሳምንት አምስት ጎሎች ከሳጥን ውጪ ተመትተው ተቆጥረዋል። ይህም በዚህ ዓመት ከፍተኛ ቁጥር ነው።

– ሌላው በሊጉ በብዛት የማይታየው በግንባር ገጭቶ ጎል ማስቆጠርም በዚህ ሳምንት ተሻሽሏል። አራት ጎሎች የተቆጠሩት በጭንቅላት ተገጭተው ነበር።

– 13 ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት ጎል አስቆጥረዋል። (በለዓለም ራስ ላይ ተመዝግበው የነበሩት ሁለት ጎሎች በዳኞች ሪፖርት ላይ በሄኖክ አየለ እና አሜ መሐመድ ተመዝግበዋል)።

– አቡበከር ናስር በሦስት ጎሎች የሳምንቱ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሲሆን ጌታነህ ከበደ ሁለት አስቆጥሮ ተከታዩ ደረጃን ይዟል። ቀሪዎቹ 11 ተጫዋቾች አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– አናጋው ባደገ፣ ተስፋዬ መላኩ፣ ቡልቻ ሹራ እና አብዱልከሪም መሐመድ የዓመቱ የመጀመርያ ጎላቸውን በዚህ ሳምንት አስቆጥረዋል።

– 11 ተጫዋቾች ለጎል በማመቻቸት አስተዋፅኦ አድርገዋል።

– ጌታነህ ከበደ እና ታፈሰ ሰለሞን በማስቆጠር እና በማቀበል ተሳትፎ ማድረግ የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው።

– አቡበከር ናስር የውድድር ዘመኑ ሦስተኛ ሐት ትሪክ ሰርቷል።

– ፋሲል ከነማ ከስድስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ አቻ ተለያይቷል።

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በዚህ ሳምንት 23 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ተመዘዋል። ይህም ካለፈው ሳምንት በሰባት ያነሰ ነው።

– እንደባለፈው ሳምንት ሁሉ ሁለት ተጫዋቾች ቀይ ካርድ ተመልክተዋል። ደስታ ጊቻሞ እና ፈቱዲን ጀማል የካርድ ሰለባዎች ናቸው።

– ፈቱዲን ጀማል ለሁለተኛ ጊዜ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ይህም በዚህ ዓመት የመጀመርያው ተጫዋች ያደርገዋል።

– ዳንኤል ደምሴ በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ቢጫ ካርድ በመመልከት ቀጣይ ጨዋታ የሚያልፈው ተጫዋች ሆኗል።

የሳምንቱ ስታቶች

(ቁጥሮቹ የተገኙት ከሱፐር ስፖርት ነው)

ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ

ከፍተኛ – ቡና እና ጊዮርጊስ (11)
ዝቅተኛ – ጅማ አባ ጅፋር (1)

ጥፋቶች

ከፍተኛ – ፋሲል፣ ድሬዳዋ እና ሀዋሳ (29)
ዝቅተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (9)

ከጨዋታ ውጪ

ከፍተኛ – ሀዲያ ሆሳዕና (12)
ዝቅተኛ – አዳማ ከተማ (0)

የማዕዘን ምት

ከፍተኛ – ጊዮርጊስ፣ ሀዋሳ እና ድሬዳዋ (6)
ዝቅተኛ – ጅማ አባ ጅፋር (1)

የኳስ ቁጥጥር ድርሻ

ከፍተኛ – ኢትዮጵያ ቡና (65%)
ዝቅተኛ – አዳማ ከተማ (35%)


© ሶከር ኢትዮጵያ