ጅማ አባጅፋር ሁለት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማምቷል

በሁለተኛ ዙር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተጠናከረው ለመምጣት ያለሙት ጅማ አባጅፋሮች ሁለት የጋና ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው መቀላቀላቸው ታውቋል።

ከቀናት በፊት አዲስ አሠልጣኝ የሾሙት ጅማ አባጅፋሮች በትላንትናው ዕለት የተከላካይ አማካዩን አማኑኤል ተሾመን ለማስፈረም መስማማታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ቡድኑ ሁለት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ለማስፈረም መስማማቱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው የመጀመሪያው ተጫዋች ጋናዊው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ራሂም ኦስማኖ ነው። በቡይልድ ኮን፣ ሙፍሪራ ወንድረርስ እና ዜስኮ ዩናይትድ ተጫውቶ ያሳለፈው ኦስማኖ ጥር ወር ላይ ወደ አልጀሪያው ኤስኦ ችሌፍ ተዛውውሮ የነበረ ቢሆንም ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ተለያይቶ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የጅማ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ የውጪ ዜጋ ፈራሚ በመሆን ቡድኑን በይፋ መቀላቀል ችሏል፡፡

ሁለተኛው ጅማ አባጅፋርን የተቀላቀለው ተጫዋች አሌክስ አሙዙ ነው። የቀድሞ የአርባ ምንጭ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ተጫዋች የነበረው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ አሌክስ አሁን የተቀላቀለውን ጅማንም ከዚህ ቀደም ማገልገሉ ይታወሳል። አሁንም ዳግም ቡድኑን በመቀላቀል በሊጉ ሁለተኛው ከፍተኛ ግብ ያስተናገደውን የቡድኑን የተከላካይ መስመር ለማጠናከር ስብስቡን ተቀላቅሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ