ሪፖርት | ወላይታ ድቻ የመጀመሪያውን ዙር በጣፋጭ ድል አገባዷል

የ13ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር የሆነው የሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በጦና ንቦቹ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተገባዷል።

ጅማ አባጅፋርን በመግጠም አዲስ ስራቸውን የጀመሩት የሲዳማው አሠልጣኝ ገብረመድህን በ12ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከተሸነፉበት የመጀመርያ 11 ፍቅሩ ወዴሳን በመሳይ አያኖ እንዲሁም ማማዱ ሲዲቤን በአዲሱ አቱላ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ በመለያየት ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት ወላይታ ድቻዎች በቅጣት ምክንያት ባልተሰለፈው በረከት ወዴሳ በአበባየሁ ሀጅሶ ተክተዋል።

በኳስ ቁጥጥር ተሽለው ጨዋታውን የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎቸ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ በአዲሱ አቱላ የግንባር ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው መክኖባቸዋል። የሲዳማ ተጫዋቾች የመጫወቻ ሜዳ እንዳያገኙ ጥቅጥር ብለው በህብረት እየተጫወቱ የነበረው ወላይታ ድቻዎች ደግሞ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በተለይ በግራ መስመር በኩል በማፋጠን የተጋጣሚያቸውን ጊዜ ከባድ ለማድረግ ጥረዋል።

ከደቂቃ ደቂቃ እያደጉ የመጡት የአሠልጣኝ ዘላለም ተጫዋቾች በ24ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሰንዝረው ነበር። በዚህ ደቂቃም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን የመዓዘን ምት የቡድኑ አምበል ደጉ ደበበ ራሱን ነፃ አድርጎ በመገኘት ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶታል። ይህንን አስደንጋጭ ሙከራ ያደረገው ደጉ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ሌላ የመዓዘን ምት በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር የሞከረውን ኳስ የግብ ዘቡ መሳይ አያኖ አክሽፎታል።

ከሁለቱ ለግብነት ከቀረቡ የግብ ሙከራዎች በኋላ ለመነቃቃት የሞከሩት ሲዳማዎች የመስመር ላይ ተጫዋቾቻቸውን በመጠቀም የድቻን ግብ መጎብኘት ይዘዋል። በዚህም በ27ኛው ደቂቃ አዲሱ አቱላ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከሳጥን ውጪ በሞከረው ኳስ ግብ መፈለጋቸውን ቀጥለዋል።

በፈጣን እና ባነሰ የኳስ ንክኪ ወደ ሳጥን መደረሳቸውን ያላቆሙት ድቻዎች በ33ኛው ደቂቃ ሌላ አስቆጪ ዕድል አምክነዋል። በዚህም ከመሐል ሜዳ በተከላካዮች መሐል የተላከውን ኳስ በሚገባ የተቆጣጠረው እድሪስ ኳሱን ለቢንያም አቀብሎት ቢንያም ዕድሉን አምክኖታል።

የፈጠራ አቅማቸው ተቀዛቅዞ የታየው ሲዳማ ቡናዎች ከመስመር ለመስመር ጥቃቶቻቸው እና ከተሻጋሪ ኳሶቻቸው ውጪ እምብዛም የፈጠራ ሀሳብ ሳይኖራቸው አጋማሹን አገባደዋል። በተቃራኒው ግብ ካለማስቆጠራቸው ውጪ የሚፈልጉትን በሜዳ ላይ እያገኙ የሚመስለው ወላይታ ድቻዎች የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ ተቆጣጥረው በሚሰነዝሯቸው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች አስፈሪ ሆነው የመጀመሪያውን አጋማሽ አገባደዋል።

ፍጥነት በተሞላው እንቅስቃሴ የሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች ገና ደቂቃዎች ሳይሄዱ ወደ ግብ መድረስ ጀምረዋል። በ47ኛው ደቂቃም ቡድኑ በቀኝ መስመር ላይ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል ደርሶ በእድሪስ አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ፈፅመዋል። ይህንን ሙከራ ካደረጉ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በግራ መስመር ተከላካዩ አናጋው ባደግ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ ኳስ ለማስጣል በእንቅስቃሴ ውስጥ የነበረው አናጋው ሳይታሰብ ወደ ግብ የመታት ኳስ መረብ ላይ አርፏል።

አጋማሹ በተጀመረ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ ያስተናገዱት ሲዳማዎች የአጥቂ መስመር ተጫዋቾችን ለውጠው በማስገባት የማጥቃት ሀይላቸውን አጠናክረው ጨዋታውን ቀጥለዋል። ተከታታይ ለውጦችን ካደረጉ በኋላም በአዲሱ የ60ኛ ደቂቃ የርቀት ኳስ እንዲሁም በሀብታሙ የግንባር ኳስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። በተጨማሪም በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ዳዊት አማካኝነት ከሳጥን ውጪ በተመታ ኳስ የመክብብን መረብ ፈትሸዋል።

ያገኙትን ሦስት ነጥብ አስጠብቀው ለመውጣት ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው መጫወት የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ሲሰነዘሩ የነበሩ ጥቃቶችን በመመከት ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ተጫውተዋል። ሲዳማዎች ደግሞ ለማጥቃት የተሻለ ፍላጎት በማሳየት ግብ ለማስቆጠር መታተር ቀጥለዋል። ለማጥቃት የራሳቸውን የሜዳ ክልል ለቀው የወጡት ሲዳማዎች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ሲጥሩ በሰሩት ጥፋት ተጫዋች በቀይ ካርድ አጥተዋል። በዚህም በ89ኛው ደቂቃ የቡድኑ አምበል የሆነው ፈቱዲን በሁለት ቢጫ ከጨዋታው ተሰናብቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በወላይታ ድቻ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ያገኙት ወላይታ ድቻዎች ያገኙትን ነጥብ 14 በማድረስ ወደ ስምንተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል። በተቃራኒው ሦስተኛ ተከታታይ ሽንፈታቸውን ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች ባሉበት የወራጅ ቀጠና ውስጥ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ