የአሠልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 0-1 ወላይታ ድቻ

የአንደኛ ዙር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ መርሐ-ግብር ከሆነው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው?

በጨዋታው ቀድመን ያሰበነውን ነገር ሙሉ ለሙሉ ተግብረናል ብዬ መናገር አልችልም። ብልጭ ድርግም የሚሉ ነገሮች ነበሩ። በጨዋታው መጀመሪያ ላይ እንዳሰብነው እንጫወት ነበር። ከዛ ግን ተጫዋቾቼ ወደ ለመዱት አጨዋወት ተመልሰዋል። ስለዚህ የምንፈልገውን በጨዋታው አላረግንም።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን የማጥቃት አጨዋወት?

በእኛ አጨዋወት ሊሆን ይችላል እነሱ በደንብ ማጥቃት ያልቻሉት። በተለይ ግብ ካገባን በኋላ አጨዋወታችን ሙሉ ለሙሉ መከላከል ነበር። ነገርግን በመልሶ ማጥቃት የሚሄዱትን ኳሶች ለመጠቀም የነበረን ጥረት ደካማ ነበር።

በሁለተኛው ዙር ቡድኑ መጠናከር ስላለበት ቦታ?

እንደሚታወቀው መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ውጤት ትንሽ ደከም ያለ ነበር። ነገርግን ቡድኑን እየጠጋገንን ውጤት ለመያዝ ጥረናል። ይህም ተሳክቶልናል። በሁለተኛው ዙር ግን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነን መቅረብ ይኖርብናል። በተለይ ከግብ ጠባቂው ጀምሮ በሚገኘው ቀጥታ የሜዳ ክፍል ትንሽ ክፍተት አለብን። በእነዚህ የሜዳ ክፍል ላይም የሚያስፈልጉንን ተጫዋቾች አዘዋውረን ጨርሰናል።

ስለ ዝውውር መስኮቱ?

ሰባት ተጫዋቾች የወላይታ ዲቻን መለያ ይለብሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሚመጡትንም ተጫዋቾች ካሉት ጋር አጣምረናቸው ጠንካራ ቡድን እንገነባለን ብለን እናስባለን።

ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው?

እንደጠበኩት አልነበረም። ጨዋታውን ተቆጣጥሮ የመጫወት ነገራችን ደካማ ነበረ። የምንቀባበላቸው ኳሶችም ለተጋጣሚ ቡድን የተጋለጡ ነበሩ። በአጠቃላይ ግን በስህተትም ቢሆን ግብ የተቆጠረብን በጨዋታው ደካማ ነበርን። ደካማ ስለሆንም ነው ማሸነፍ ያልቻልነው። ለሚቀጥለውም ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።

ተጋጣሚ ቡድን ስለተከተለው የጨዋታ መንገድ?

የተጋጣሚ ቡድን አሠልጣኙ ከጨዋታው በፊት ባሉት መንገድ አልነበረም ግቡ የተቆጠረብን። ሲፈጠሩ የነበሩ አጋጣሚዎችም በተባለው መንገድ አልነበሩም። ነገርግን በመልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ ጥሩ ናቸው። እኛ በተቻለን መጠን በራሳችን ሜዳ ላለመቆየት ጥረት ስናደርግ ነበር። ነገርግን የኳስ ቅብብላችን ጥሩ አልነበረም። የአቅም ውስንነትም ይታያል። ስለዚህ በሁለተኛ ዙር በጣም መስራት ይጠበቅብናል።

በቀይ ካርድ ከሜዳ ስለወጣው የቡድኑ አምበል ፈቱዲን?

ተጫዋቹ የወሰነው ደካማ ውሳኔ ነው። ለወደፊትም መሻሻል አለበት።

በሁለተኛው ዙር ቡድኑ መጠናከር ስላለበት ቦታ?

መሻሻል ያለባቸው ቦታዎች አሉ። አንዱ የአጥቂ መስመራችን ላይ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ደካማውን የመስመር ላይ አጨዋወታችንን ለማጠናከር የመስመር ተጫዋች ያስፈልገናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ