ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ13ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ13ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጠናል።
አሰላለፍ : 4-3-3

ግብ ጠባቂ

መሐመድ ሙንታሪ – ሀዲያ ሆሳዕና

በጨዋታ ሳምንቱ አራት ቡድኖች ግብ ሳያስተናግዱ ጨዋታቸውን መጨረስ ችለዋል። ሆኖም ግን ግብ ጠባቂዎቻቸው በበርካታ ሙከራዎች ተፈትነው ነበር ማለት ይከብዳል። በንፅፅር ካየነው ሙንታሪ በሁለት አጋጣሚዎች ጅማ አባ ጅፋር ግብ ሊያስቆጥር የሚችልባቸውን ቅፅበቶች ከማምከኑ አንፃር በተሻለ ነጥብ የሳምንቱ ምርጥ ውስጥ አካተነዋል።

ተከላካዮች

ዱላ ሙላቱ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያ ሆሳዕና እጅግ በሳሳ የቡድን ስብስብ ጅማ አባ ጅፋርን በገጠመበት ጨዋታ በቀኝ መስመር አማካይነት የጀመረው ዱላ ሙላቱ በሁለተኛው አጋማሽ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ውሳኔ ወደ ቀኝ መስመር ተከላካይነት ተዘዋውሮ ተጫውቷል። ዱላ እንደመስመር አማካይነቱ ሁሉ ወደ ኋላ ተስቦም አብዛኛውን ጊዜውን በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲያሳልፍ የቆየ ሲሆን የቡድኑ አብዛኛው ጥቃት በእርሱ አቅጣጫ አመዝኖ ቆይቶ ብቸኛዋ ግብ ስትቆጠርም እንዲሁ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።

ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ

አንጋፋው የመሐል ተከላካይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ባሳየው ጠንካራ ብቃት ለሁለተኛ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ እንዲካተት ሆኗል ። ተጫዋቹ ቡድኑን ከኋላ ሆኖ በመምራት፣ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በማቋረጥ እንዲሁም ቡድኑ የሚያገኛቸውን የቆሙ ኳሶችን ለመጠቀም የሚጥርበት መንገድ እጅግ ጥሩ ነበር። በተለይም በጨዋታው ሁለት ከመዓዘን የተሻገሩ ኳሶችን በእግሩ እና በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሮ የግቡ አግዳሚ እና ግብ ጠበቂው ያመከኑበት አጋጣሚ የሚታወሱ ነበሩ።

አንተነህ ተስፋዬ – ሰበታ ከተማ

ቀልጣፋው የመሀል ተከላካይ አንተነህ ቡድኑ የሊጉን መሪ ፋሲል ከነማን ገጥሞ አቻ ሲወጣ ጥሩ ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ ከአጣማሪው መሳይ ጋር በመሆን የሊጉን ሁለተኛ ግብ አስቆጣሪ ሙጂብን የተቆጣጠረበት እና ጥቃቶች መሐል ለመሐል እንዳይሰነዘሩ የጣረበት ብቃት ድንቅ ነበር። በተጨማሪም ቡድኑ ኳስ ከኋላ መስርቶ እንዲጫወት የአንተነህ የኳስ ቅብብሎች ወሳኝ ነበሩ።

አብዱልከሪም መሐመድ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈጣኑ እና ታታሪው የመስመር ተከላካይ አብዱልከሪም ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን 4-3 ሲያሸነፍ ያሳየው ብቃት ድንቅ ነበር። ተጫዋቹ በቦታው ከሚጠበቅበት የመከላከል ብቃት በተጨማሪ ያሳየው የማጥቃት እንቅስቃሴ አድናቆት የሚያስቸረው ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይም እጅግ ለግብነት የቀረበ ኳስ ከመሞከሩ በተጨማሪ የቡድኑን መሪነት ወደ አራት ከፍ ያደረገች ጎል ከመረብ አሳርፏል።

አማካዮች

ዳዊት እስጢፋኖስ – ሰበታ ከተማ

እርግጥ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ ጎልቶ የወጣ ተጫዋች ባይኖርም አልፎ አልፎ በዚህ የጨዋታ ሚና የሚጫወተውን እና በዚህኛው ጨዋታ ጥሩ የነበረውን ዳዊትን በቦታው ለመጠቀም ተገደናል። በተለይም ዳዊት ቡድኑ ኳስ ተቆጣጥሮ በሚጫወትበት ወቅት ቁልፍ ቁልፍ የኳስ ቅብብሎችን በመፈፀም በጨዋታው የተሻለ ተንቀሳቅሷል። ቡድኑ የግብ ማግባት አማራጮች ባጣበት ጊዜ ከሚልካቸው የፊትዮሽ ኳሶች በተጨማሪም ከሳጥን ውጪ ግብ ለማስቆጠር ሲሞክር ተስተውሏል። ቡድኑም አቻ ሲወጣ ለቡልቻ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ዳዊት ነበር።

ካሉሻ አልሀሰን – ሀዲያ ሆሳዕና

ጋናዊው የሀዲያ ሆሳዕና አማካይ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ መካተት ችሏል። በባለፈውም ሆነ ባሁኑ ጨዋታ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ዘግይቶ በመድረስ ሙከራዎችን የሚያደርግበት ጥረት ሰምሮለት ቡድኑ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰበትን ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል። ታታሪነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣው ካሉሻ ከጅማ ጋር በነበረው ጨዋታ እንደወትሮው ሁሉ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በዋነኝነት ሲመራም ውሎ ነበር።

ታፈሰ ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና

በኢትዮጵያ ቡና አማካይ ክፍል ውስጥ ሲለወጥ የማይታየው ታፈሰ ሰለሞን ድንቅ የጨዋታ ቀን ማሳለፍ ችሏል። ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ ከፈጠራቸው ዕድሎች በሁለቱ ላይ ተካፋይ የነበረው ታፈሰ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያውን የአቡበከር ናስርን ጎል አመቻችቶ ሲያቀበል የቡድኑን አራተኛ ግብ ደግሞ በድንቅ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል። ዘንድሮ ታታሪነትን ተላብሶ የመጣው አማካዩ በቡድኑ የኳስ ምስረታ ሂደት ውስጥ ዋነኛ ማዕከል ሆኖ የዋለበት እንቅስቃሴ በውጤታማነት በመታጀቡ የማያከራክር ምርጫ ለመሆን ችሏል።

አጥቂዎች

ቡልቻ ሹራ – ሰበታ ከተማ

ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ግብ አስቆጣሪነት የተመለሰው ቡልቻ በ13ኛ ሳምንት ከታዩ ምርጦች መካከል አንዱ ነው። በግራ መስመር አጥቂነት ተሰልፎ የፋሲል ተከላካዮችን ሲረብሽ የታየው ቡልቻ በጨዋታው ፍጥነቱን ተጠቅሞ ሲያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች አደገኛ ነበሩ። በጨዋታውም ቡድኑን አቻ ያደረገ ኳስ ወደ ግብነት ሲቀይር ራሱን ነፃ አድርጎ የሩቁ ቋሚ ላይ በመገኘት ዳዊት ያሻገረውን የቆመ ኳስ የተጠቀመበት መንገድ ጥሩ ነበር።

አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

ከጨዋታ ሳምንቱ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው የነበረው አቡበከር ናስር በሳምንቱ ምርጥ ውስጥ መካተቱ የሚያስገርም አይሆንም። በግማሽ የውድድር ዓመት ለሦስተኛ ጊዜ ሐት – ትሪሆክ በሰራበት ጨዋታ ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ባለ ድል እንዲሆን አድርጋል። በግንባር ፣ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ከመጨረሻ ተከላካይ ኋላ ተነስቶ አስገራሚ ፍጥነቱን ባሳየበት አኳኋን ያስቆጠራቸው ግቦችም የተጨዋቹ ግብ የማስቆጠሪያ መንገዶችን መበራከት ያሳየ ነበር።

ጌታነህ ከበደ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የ13ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ 11 ተጫዋቾችን በአጥቂነት የሚመራው ተመራጫችን ጌታነህ ከበደ ነው። ከጨዋታ ጨዋታ እጅግ ጥሩ እየሆነ የመጣው ጌታነህ ቡድኑ በወልቂጤ እየተመራ በቶሎ ወደ ጨዋታ እንዲገባ ያስቻለ ኳስ ከቅጣት ምት እንዲሁም መሪ የሆነበትን ኳስ በግንባሩ ከመረብ በማገናኘት ጥሩ ጊዜን አሳልፏል። በተጨማሪም ወደ ኋላ እየተመለሰ ተካላካዮችን በእንቅስቃሴ እና በኳስ ቅብብል ለመሳብ የሚያደርገው ጥረት በጨዋታው ጎልቶ እንዲወጣ አስችሎታል።

አሰልጣኝ

ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

በሳምንቱ ከተደረጉ ጨዋታዎች ውስጥ ከደረጃ ሰንጠረዥ ባለፈም እንደ ክለብ የቅርብ ተፎካካሪ የሆኑት ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻን ካገናኘው ጨዋታ ቡድናቸው ሙሉ ነጥብ እንዲያሳካ የአሰልጣኝ ዘላለም ድርሻ ከፍ ያለ ነበር። ከወትሮው በተሻለ የማጥቃት ድፍረት ወደ ሜዳ የገባው ቡድናቸውን በውስን ተቀያሪ ተጨዋቾች አደራጅተው ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካታቸው አሰልጣኙን ኮከብ አስብሏቸዋል።

ተጠባባቂዎች

መክብብ ደገፉ – ወላይታ ድቻ

ላውረንስ ላርቴ – ሀዋሳ ከተማ

አናጋው ባደግ – ወላይታ ድቻ

ዳዊት ታደሰ – ሀዋሳ ከተማ

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ኢትዮጵያ ቡና

ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ

ቢኒያም ፍቅሬ – ወላይታ ድቻ


© ሶከር ኢትዮጵያ