የቀድሞው እና የዘመኑ ድንቅ አጥቂዎች በስልክ ምን አወሩ…?

የቀድሞው ታላቅ አጥቂ ዮርዳኖስ ዓባይ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እጅግ አስደናቂ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ወጣቱ አጥቂ አቡበከር ናስር ጋር ስልክ ስለመደወሉ እና ምን እንዳወሩ ለሶከር ኢትዮጵያ ይናገራል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ጎልተው ከወጡ የጎል አነፍናፊ አጥቂዎች መካከል አንዱ የነበረው ዮርዳኖስ ዓባይ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት (ከ1993 እስከ 95) ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ከማጠናቀቁ በሻገር በ1993 የውድድር ዘመን በ24 ጎል በ2009 በጌታነህ ከበደ እስከተሰበረበት ጊዜ ድረስ በአንድ ዓመት በርካታ ጎሎች በማስቆጠር ለረጅም ጊዜ ባለታሪክ እንደነበር ይታወሳል። ከኢትዮጵያ አልፎ በየመን በነበረው ቆይታም የሊጉ 3 ጊዜ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ እና የክለቡ አልሳቅር 8 ጊዜ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች የሆነው “ቡሎ” በወጣት እና ዋናው ብሔራዊ ቡድንም ድንቅ ጊዜያትን አሳልፎ ጫማውን ከሰቀለ በኃላ ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ በመቀላቀል በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሊግ እየተሳተፈ ለሚገኘው መከላከያ በምክትል አሰልጣኝነት እየሰራ ይገኛል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ብዙ ባልተለመደ ሁኔታ ዮርዳኖስ ዓባይ የወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ መነጋገሪያ ዕርስ በመሆን አስደናቂ የውድድር ዓመት እያሳለፈ ለሚገኘው ወጣቱ አጥቂ አቡበከር ነስር ጋር ደውሎለት ነበር። ይህ ክስተት ስለተፈጠረበት ምክንያት ለማወቅ ብለን ዮርዳኖስን አግኝተነው አቡበከር ጋር ለመደወል ስላበቃው ምክንያት ምላሽ እንዲሰጠን ጠይቀነው ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቶናል።

” የዘንድሮ ፕሪምየር ሊግን የመከታተል ዕድሉን በስፋት አግኝቻለው። እንደ አበቡበከር ናስር ያለ ወጥ አቋሙን ጠብቆ የዘለቀ ተጫዋች አላየሁም። ለጎል ያለው ቅርበት፣ የአጨራረስ ብቃት፣ ከኳስ ጋር ያለው ክህሎቱ አስራ ስድስት ከሀምሳ ውስጥ የሚያደርገው ነገር፣ በአጠቃላይ የአጥቂነት ባህሪው የተለየ ጥሩ ነገር ነው ያየሁበት። በዚህ ዕድሜው ይሄን ሁሉ ሲያደርግ በጣም ነው የተገረምኩት። እንድያውም ወደ ኃላ ሀያ ዓመት ተጉዤ በወጣትነት እድሜዬ ኤልፓ እና ቡና በነበርኩበት ዘመን የማደርገውን እንቅስቃሴ በትዝታ ነው የመለሰኝ። እኔ የማደርገውን እንቅስቃሴ በእሱ ውስጥ አየሁበትና ራሱ ጋር ደውዬ የሚሰማኝን ስሜት ላወራው የፈለኩት።

” ደውዬ የነገርኩት የአደራ መልዕክት ነው። ‘ትልቅ ኃላፊነት አለብህ ብዙ ይጠበቅብሀል፣ ብዙ መሥራት አለብህ። ስለዚህ ከአሁኑ ዝግጅት ማድረግ አለብህ። ራስህን በሁሉም ነገር ጠብቅ’ ብዬዋለው። ‘እንደሚታወቀው ትንሽ ነገር ሲያገኙ በሰዎች እየተመሩ ብዙ ልጆች አጥተናል፤ ጠፍተዋል። ስለዚህ ጠንክረህ ስራ አንተን የሚከተሉ ብዙ ታዳጊዎች አሉ። ለእነርሱ አርዓያ መሆን አለብህ። ከዚህ በተሻለ ከሀገር ውጭ መጫወት አለብህ። አሁን ካለህ የሰውነት አካል ብቃትም መጨመር አለብህ። በአጠቃላይ ለአንተ እድገት የዛሬዋ ቀን ወሳኝ ስለሆነች በርታ’ ብየዋለሁ። አቡበከርም በምላሹ ‘በጣም አመሰግናለሁ’ ብሎኛል። እኔ መደወሌን ፈፅሞ አልጠበቀም እና አመስግኖ አክብሮቱን ገልፆልኛል።

” ብዙ ጨዋታውን አይቻለሁ። እንግዲህ ደውሎ እርሱን ለመምከር ያነሳሳኝ አንደኛ እኔን ወደ ኃላ ስላስታወሰኝ እና የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ካለኝ መልካም ሀሳብ ነው። ለመደወልም ለመምከርም የፈለኩት። በዚህም ብቻ አላበቃሁም። ከደወልኩለት ከ30 ደቂቃ በኃላ በግል ፌስቡክ ገፄ ላይ ‘ቡና እና መብራት ኃይል ያደረኩትን አቡበከር በትዝታ ወደ ኃላ መለሰኝ። እኔ በሜዳ ላይ የማድርገውን እንቅስቃሴ እርሱ ላይ አየሁበት። በጣም የሚገርም አጥቂ ነው። ይህን ይዞ ለማስቀጥል ትልቅ ኃላፊነት እና አደራ አለብህ አላህ ይርዳህ’ ብዬ ፅፌያለሁ።

” አቡበከር ሪከርዱን የመስበር ዕድል አለው። ምክንያቱም እያገባ ነው። አንዳንዴ ብዙ የጎል አጋጣሚ አግኝተህ የማታገባ ከሆነ ላይሰብረው ይችላል ትላለህ። ሆኖም የሚያገኘውን አጋጣሚ ሁሌ ወደ ጎልነት የሚቀይር ከሆነ ለምን አይሰብረውም። ከዛም በላይ ማድረግ ይችላል። አንድ አጥቂ ሁሌ እያገባ የሚሄድ ከሆነ እየቀለለው ነው የሚሄደው አቡበከርም በራስ መተማመኑ እየጨመረ ነው የሚሄደው። እንደ አጋጣሚ ቡድኑ እያሸነፈ ነው። አንድ አጥቂ ጎል እያገባ ቡድኑ የሚሸነፍ ከሆነ የእርሱ ብቻ ጎል ማግባት አይጠቅመውም። ስራውንም ከባድ ያደርግበታል። አቡበከር ደግሞ ቡድኑ እያሸነፈ የሚሄድ መሆኑ የእርሱ ብቃት ተጨምሮ ሪከርዱን የመስበር ሰፊ ዕድል አለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ