ያለግብ አቻ ከተጠናቀቀው የ4 ሰዓት ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ከአሰልጣኞች ተቀብሏል።
ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ
ስለ ጨዋታው?
እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ጥሩ ነው። ነገርግን የተወሰኑ የምንሰራቸው ነገሮች እንዳሉ የሚያሳይ ነበር። ኳስ ስንይዝ እና ስናጣ የምናደርገው ነገር ላይ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ። እነዚህን በሂደት የምናስተካክላቸው ይሆናል። ግን ሦስት ልምምድ ብቻ ሰርቶ ለቀረበ ቡድን ውጤቱ በቂ ነው ብዬ አስባለሁ።
ቡድኑ ስለነበረው የሁለተኛ አጋማሽ ብቃት?
ቡድኑ ካለበት ደረጃ አንፃር ጨዋታዎችን ማሸነፍ ያስፈልገናል። ለዛም ነው በሁለተኛው አጋማሽ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾችን አስገብተን የነበረው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን አልተሳካልንም። በቀጣይ ጨዋታዎች ግን ይህንን ለማሳካት በርትተን እንሰራለን።
ቡድኑ መሻሻሎችን ማድረግ ስላለበት ቦታ?
ኳስ ስንይዝ መስተካከል ያለበት ነገር አለ። ስለዚህም መሐል ሜዳ ላይ የምናስተካክለው ነገር ይኖረናል። በአጥቂ መስመር ላይ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች አሉን። በእነሱ ላይ ሰርተን ስል ለመሆን እንሞክራለን።
ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ
ስለ ጨዋታው?
አንዳንድ ጊዜ የጠበካቸው ነገሮች አይሆኑም። ያልጠበካቸው ነገሮች ደግሞ ይሆናሉ። ከጠንካራ ቡድኖች ጋር ጠንካራ እንሆናለን። በውጤታቸው ትንሽ ዝቅ ያሉ ክለቦችን ስንገጥም ደግሞ አመለካከታችን ጥሩ አይሆንም። ነጥብ የጣልነውም በደረጃ ሰንጠረዡ ታች ባሉ ክለቦች ነው። አቅሙ ስላለን ግን ከዚህም በላይ መሄድ እንችላለን ብዬ አምናለሁ።
በሁለቱ አጋማሾች ስለነበረው እንቅስቃሴ?
ከመጀመሪያ ጀምሮ እንቅስቃሴዎቹ ክፍት ነበሩ። ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ ውጤትን ለማስጠበቅም ሊሆን ይችላል ጥፋቶች ይበዙበት ነበር። በዚሁ አጋጣሚ ዳኞች ተጫዋቾች ላይ ክትትል ቢያደርጉ እና ተጫዋቾችን ቢንከባከቡ ጥሩ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጥፋቶቹ ከባዶች ነበሩ። ይሄ ነገር ለእኔ ቡድን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሊጉ ቡድኖች ቢሆን መልካም ነው።
ቡድኑ ማሻሻል ስላለበት ነገር?
ለሁሉም ክለብ አንድ አይነት አመለካከት እንዲኖረን በአምሮ ረገድ ለመስራት እንሞክራለን። በተጨማሪም የአጨራረስ ድክመታችን ላይ ሰርተን በሁለተኛው ዙር ለመምጣት እንሞክራለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ