ሪፖርት | ድሬዳዋ እና ሰበታ ነጥብ ተጋርተዋል

በመጀመሪያው አጋማሽ አራት ጎሎች የተስተናገደበት የረፋዱ ጨዋታ በ2-2 አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከሀዋሳው ጨዋታ ኢታሙና ኬይሙኒን በእንዳለ ከበደ ምትክ ሲጠቀም ሰበታ ደግሞ ከፋሲል ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ታደለ መንገሻን በዳንኤል ኃይሉ እና ያሬድ ሀሰን በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የጨዋታ ፉክክር እና አራት ግቦችን አስመልክቶናል። በሙከራ ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ድሬዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ የአስቻለው ግርማ የርቀት ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶባቸዋል። የተለመደው የተከላካይ ክፍል መዘናጋታቸው በታየበት ሁኔታ ግን ፍፁም ገብረማርያም 10ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ሀሰን ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት የተጀመረን ኳስ በግሩም ሁኔታ አሻግሮለት ጎል አስቆጥሮባቸዋል። 17ኛው ደቂቃ ላይ ከሌላ ቅጣት ምት በዳዊት እስጢፋኖስ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት ሰበታዎች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ ቢሆኑም የድሬዎችን በጥንቃቄ የተሞላ የመሀል ክፍል አልፈው መግባት ቀላል አልሆነላቸውም።

ኳስ በማቋረጡ ጥሩ የነበሩት ድሬዎችም የመጨረሻ ኳሶቻቸው እየተበላሹ ከሙከራ ርቀው ቢቆዩም 24ኛው ደቂቃ ላይ ከኋላ በቀጥታ በተላከ ኳስ ግብ አግኝተዋል። ያሬድ ዘውድነህ መሬት ለመሬት የላከለትን ኳስ ከመሐል ሜዳ ጀምሮ እየገፋ በመሄድ ጁኒያስ ናንጄቦ ነበር ቡድኑን አቻ ያደረገው። በዕለቱ ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ሳቢያ የውሀ ዕረፍት የተሰጠበት ጨዋታው በተመጣጣኝ ፉክክር የቀጠለ ሲሆን 37ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ድሬዎች የሰሩት ስህተት ፍፁም ሌላ ጎል እንዲያስቆጥርባቸው አድርጓል። 

በረጅኙ ወደ ግብ ክልላቸው የመጣውን ኳስ በአግባቡ ሳያቋርጡት በግቡ አግዳሚ ሲመለስ አግኝቶ ነበር ፍፁም ሰበታን ዳግም መሪ ያደረገው። ሆኖም ከዕረፍት በፊት 43ኛው ደቂቃ ላይ የሄኖክ ኢሳይያስ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል ጨዋታውን ወደ 2-2 ሊይመጣው ችሏል። ጁኒያስ ናንጄቦ ከዘነበ ከበደ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ መጠቀም ሳይችል ቀርቶ ነው እንጂ ብርቱካናማዎች ጨዋታውን የመመራት ዕድልም አግኝተው ነበር።

የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች በሰበታ ከተማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢቀጥልም ከመጀመሪያው በተቃራኒ ሙከራዎች ሊታዩ አልቻሉም። የሰበታዎች የተሻሉ ጥረቶችም ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ ከውጤታማነት ርቀው ቆይተዋል። በሂደት በተለይም ሪችሞንድ ኦዶንጎ በአስቻለው ግርማ ተቀይሮ መግባት በኋላ ድሬደዋ ከተማዎች የሰበታን የኳስ ቁጥጥር ተቋቁመው ፈጠን ባሉ ሽግግሮች አልፎ አልፎ ከመሀል ሜዳ ሲሻገሩ ቢታዩም ፊት መስመር ላይ ያላቸው ደካማ ቅንጅት ተጋጣሚያቸውን ጫና ውስጥ መክተት ተስኗቸው ታይተዋል።

ጨዋታው በድጋሚ ለውሀ ዕረፍት ጊዜ ተሰጥቶበት ቀጥሎ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከባድ ሙከራዎች አስተናግዷል። 86ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ጊዜ በተከታታይ ቡልቻ ሹራ ከባድ ሙከራዎችን ሲያደርግ በግንባሩ የሞከረው ወደ ውጪ ሲወጣ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ አክርሮ የመታውን ኳስ ፍሬው ጌታሁን አድኖበታል። ድሬዳዋ ከተማዎችም ከመልሶ ማጥቃት እና ከቆሙ ኳሶች ምላሽ ለመስጠት ሞክረው ሳይሳካላቸው ጨዋታው 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ